በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን በገዜ ጎፋ ወረዳ በኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ከትናንት በስቲያ በደረሰ የመሬት ናዳ አደጋ የሞቱ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ ነው።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በመሬት ናዳ ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ የመጣ ሲሆን እስከ ትንናት ምሽት ድረስ የሟቾች ቁጥር 229 ነበር።
የገዜ ጎፋ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ምስክር ምትኩ የሟቾች ቁጥር ወደ 260 ማሻቀቡን ተናግረዋል።
እስካሁን በተደረገው ፍለጋ ሴቶችና ሕፃናትን ጨምሮ በድምሩ የ260 ሰዎች አስክሬን የተገኘ ሲሆን፣ የአስክሬን ፍለጋ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
የሟቾች ቁጥር ከዚህ በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችልና የነፍስ አድን ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
አደጋው መጀመሪያ ሶስት ቤተሰብ ላይ መድረሱን ያስታወቁት በገዜ ጎፋ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ምስክር ምትኩ፤ ይህንን ሰምተው እነሱን ለማዳን ጥረት እያደረጉ እያለ ድጋሚ ባጋጠመ የመሬት መንሸራተት አደጋ የበርካቶች ህይወት ማለፉን አስታውቀዋል።
በአደጋው ሰለባ ከሆኑት ሰዎች መካከል የወረዳው ፖሊስ አዛዥን ጨምሮ ሴቶችና ሕፃናት እንደሚገኙበትም አስተዳዳሪው አስታውቀዋል።
ተጨማሪ የሞቱ ሰዎች አስከሬንን ለማውጣት የክልሉ መንግስት ድጋፍ እንዲደረግለት የፌደራል መንግስትን ጠይቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላፉት መልእክት፤ “በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ድንገተኛ የመሬት ናዳ አደጋ የበርካታ ዜጎቻችንን ሕይወት ቀጥፏል፤ በደረሰው አስከፊ ጉዳት የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን እገልጻለሁ” ብለዋል።
“አደጋውን ተከትሎ የፌዴራል የአደጋ መከላከል ግብረ-ሀይል በአካባቢው ተሰማርቶ የአደጋውን ጉዳት ለመቀነስ ርብርብ እያደረገ ነው” ሲሉም አስታውቀዋል።ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ለተጎጂ ለቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን እመኛለሁ ብለዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላፉት መልእክት፤ “ከኢትዮጵያ በሰማውት ዜና እና በመሬት ናዳ ሳቢያ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ህልፈት አሳዝኖኛል” ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሚገኘው የዓለም ጤና ድርጅት ቡድን አፋጣኝ የጤና አቅርቦት ድጋፍ ለማቅረብ ወደ ስፍራው መሰማራቱንም አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የበርካታ ሀገራት መሪዎች በኢትዮጵያ በደረሰው አደጋ ዙሪያ ማዘናቸውን እየገለጹ ሲሆን ለተጎጂዎችም መጽናናትን በመመኘት ላይ ናቸው፡፡