በሺዎች የሚቆጠሩ የሶማሊላንድ ወታደሮች ለሥልጠና ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን የራስ ገዟ መንግስታዊ ቴሌቪዥን ዘግቧል፡፡
የሶማሊያ ወጣቶችን የጫኑ በርካታ ታታ መኪኖች ሲያልፉ መመልከታቸውን የድሬዳዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ የሶማሊላንድ ወታደሮች ወታደራዊ ሥልጠና ለመውሰድ ከትናንት ማክሰኞ ሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ላይ መሆናቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በመንግሥት የሚተዳደረው የሶማሊላንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ ለወታደራዊ ሥልጠና ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዙ ናቸው ያላቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ የሠራዊት አባላት በተሽከርካሪዎች ጉዞ ሲጀምሩ አሳይቷል።
“የሶማሊላንድ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሜጀር ጄኔራል ኑህ እስማኢል ለሥልጠና የሚጓዙትን ሠልጣኞች ሸኝተዋል” ብሏል መንግሥታዊው የሶማሊላንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ በዘገባው።
ወታደራዊ ሥልጠናውን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ በኩልም እንዲሁም የሠራዊት አባላቱ ቁጥር “በሺዎች የሚቆጠሩ” ከማለት ውጪ ምን ዓይነት ሥልጠና እንደሚወሰዱ የተገለጸ ነገር የለም።
ቴሌቪዥን ጣቢያው በበርካታ አውቶብሶች እና የደረቅ ጭነት ተሸከርካሪዎች ከሶማሊላንድ ተነስተው ዋጃሌ የተባለች የድንበር ከተማን አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ አሳይቷል።
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ከኢትዮጵያ እና ከሶማሊያ መንግሥታት በኩል አስካሁን የተባለ ነገር የለም።
ከስድስት ወራት በፊት የሶማሊላንድ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች አዲስ አበባ ተገኝተው በወታደራዊ ጉዳዮች ትብብር ዙሪያ ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።
ይህ በዚህ እንዳለ የቀድሞ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት አማካሪ ከኢትዮጵያ የተቃጣብንን ትንኮሳ ለመከላከል ብቸኛው አማራጭ አልሸባብ ነው ብለዋል፡፡
ሶማሊያ “በኢትዮጵያ የተቃጣባትን ጥቃት” ለመከላከል ብቸኛው የመከላከያ አማራጭ አልሻባብ ብቻ ነው ሲሉ የቀድሞ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት የደህንነት አማካሪ እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አብዲሰይድ ሙሴ አሊ ተናግረዋል።
አሁን ላይ ከኢትዮጵያ “የተቃጣብንን ጥቃት” ሊከላከልልን የሚችለው “ብቸኛው ብቃት ያለው ሀይል አልሸባብ ነው” ሲሉ አማካሪው አስታውቀዋል።
አማካሪው ከቢቢሲ ሶማሊያ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “ግዛት የማስፋፋት ፍላጎት የተጠናወታቸው” እና “ጽንፈኛ አክራሪ” ናቸው ሲሉ ኮንነዋል።
“ከአልሸባብ በስተቀር የኢትዮጵያን የመስፋፋት ትንኮሳ ሊቋቋም የሚችል የሶማሊያ ወታደራዊ ሀይል የለም” ያሉት አማካሪው የአልሸባብን ሽብርተኛ ተብሎ መጠራት እንደማይቀበሉትም ተናግረዋል።
የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ በበኩላቸው “አልሸባብን መደገፍ ሀጢያት ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ በአዲ አበባ የወደብ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡
በዚህ ስምምነት መሰረት ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና እንድትሰጥ እንዲሁም ሶማሊላንድ ደግሞ ለኢትዮጵያ የባህር ሀይል መመስረት የሚያስችላትን ወደብ ለመስጠት ተስማተዋል፡፡
ስምምነቱን ተከትሎ ሶማሊላድ የራሴ ግዛት አካል ናት የምትለው ሶማሊያ ተቃውሞዋን በይፋ የገለጸች ሲሆን በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ትገኛለች፡፡
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርክ አደራዳሪነት በአንካራ መወያየት የጀመሩ ሲሆን ሁለተኛውን ድርድር ከሁለት ወር በኋላ በአንካራ ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡