ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ከወደብ ስምምነት ውጪ በሌሎች ጉዳዮችም እየተደራደሩ መሆኑን ገለጹ

የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ በወቅታዊ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ላይ ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ጉዳይ ዋነኛው ነው።

በቱርክ አደራዳሪነት በአንካራ የተጀመረው የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ድርድር ሁለተኛው ዙር የፊታችን ነሀሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም ይቀጥላል የተባለ ሲሆን ይህ ድርድር ምን ያህል ከውጭ ጣልቃ ገብነት የተጠበቀ ነው?  የሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ተከታዩን ብለዋል።

“ኢትዮጵያ በታሪኳ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ስትደራደር ቆይታለች፣ አንድም ጊዜ በውጭ ጣልቃ ገብነቶች ጥቅሟን አሳልፋ ሰጥታ አታውቅም” ብለዋል።

“በአንካራ እየተካሄደ ያለው የሁለትዮሽ ድርድርም ብሔራዊ ጥቅማችንን ባስጠበቀ መንገድ ይቀጥላል” ያሉት አምባሳደር ነብዩ በድርድሩ ላይ ምንም አይነት ጣልቃ ገብነት እንደሌለ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ እያደረጉት ባለው ድርድር የወደብ ጉዳይ ብቸኛው አጀንዳ አለመሆኑን የተናገሩት ቃል አቀባዩ ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በተሰማራው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ወይም አትሚስ ቀጣይ ጦር አሰፋፈር ሁኔታ እና ሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ እየተደራደሩ መሆኑንም አንስተዋል።

በአንካራ በተካሄደው የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ድርድር ላይ ለሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መበላሸት መነሻ የሆነችው ሶማሊላንድ ለምን አልተሳተፈችም? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም “አለሙግባባት የተከሰተው በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል እንጂ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ሙካከል አይደለም” ሲሉም አምባሳደር ነብዩ ምላሽ ሰጥተዋል።

ከሁለት ወራት በኋላ በድጋሚ በአንካራ በሚካሄደው የሁለተኛው ዙር ድርድር ላይ ኢትዮጵያ ምን ትጠብቃለች? በሚልም ጥያቄ የተነሳ ሲሆን አምባሳደር ነብዩ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል።

” የፊታችን ነሀሴ 27 በሚካሄደው ድርድር ላይ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር የነበራት ግንኙነት ከዚህ በፊት ወደነበረው መልካም ግንኙነት እንዲመለስ የሚያደርጉ መግባባቶች ይፈጠራሉ ብለን እንጠብቃለን” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ጋር የወደብ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

ስምምነቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነት የታወከ ሲሆን ሞቃዲሾ የኢትዮጵያን አምባሳደር ለቆ እንዲወጣ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን ስትወስድ ቆይታለች።

ኢትዮጵያ በበኩሏ በሶማሊያ ለተወሰዱ እርምጃዎች ዝምታን የመረጠች ሲሆን ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት የየትኛውንም ሀገር ሉዓላዊነት እንዳልጣሰ ገልጻለች።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *