ቻይና በአማርኛ ቋንቋ ያስተማረቻቻውን የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችን በትናትናው እለት አስመርቃለች።
በቤጂንግ የውጭ ጥናት ዩኒቨርስቲ (BFSU) በትናንትናው ዕለት ተማሪዎቹን ያስመረቀ ሲሆን፤ ከተመራቂዎቹ መካከልም በአማርኛ ቋንቋ በመጀመሪያ ዲግሪ ያስተማራቸውን ተማሪዎቹ ይገኙበታል።
በቻይና የኢትዮጵያ ኤማባሲ ተወካዮች ቤጂንግ የውጭ ጥናት ዩኒቨርስቲ (BFSU) የአማርኛ ቋንቋ ተማሪዎች ምርቃት ላይ መሳተፋቸውንም ኤምባሲው አስታውቋል።
“በቤጂንግ የውጭ ጥናት ዩኒቨርስቲ (BFSU በቻይና ውስጥ ብቸኛው የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍል የሚሰጥ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፤ ትናንት ከተመረቁት መካከል የመጀመሪያው ዙር የአማርኛ ተማሪዎች ይገኙበታል ብሏል ኤምባሲው ባወጣው መረጃ።
ኤምባሲው ቤጂንግ የውጭ ጥናት ዩኒቨርስቲ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት መስጠቱን አመስግኖ፤ “ይህ የሁለቱን ሀገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ያጠናክራል” ብሏል።
የቤጂንግ የውጭ ጥናት ዩኒቨርሲቲ ለቻይናውያን ተማሪዎች የተዘጋጁ የአማርኛ መማሪያ መጽሃፍትን ባሳለፍነው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በቤጂንግ የውጭ ጥናት ዩኒቨርስቲ (BFSU) አማርኛ ቋንቋን በመጀመሪያ ዲግሪ ማስተማር መጀመሩን ይፋ ያደረገው በፈረንጆቹ 2022 ላይ ነበር።
ዩኒቨርስቲው ከቀዳሚ የቻይና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል አንዱ ነው።
ዩንቨርሲቲው ሃይዲያን በተሰኘው የቤጂንግ አካባቢ የሚገኝም ሲሆን ምስራቅና ምዕራብ ብለው የተከፈሉ ሁለት ካምፓሶች አሉት።
ተጠሪነቱ በቀጥታ ለሃገሪቱ ትምህርት ሚኒስቴር የሆነው ዩኒቨርስቲው በአሁኑ ሰዓት አማርኛን ጨምሮ በ101 የውጭ ሃገራት ቋንቋዎች በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች ያስተምራል።
የአማርኛ ቋንቋ ከሩሲያ እና ቻይና በተጨማሪ በአሜሪካ፣ ጀርመን እና ሌሎችም ሀገራት በመሰጠት ላይ ሲሆን ኢትዮጵያም የተለያዩ ሀገራት ቋንቋዎችን ለዜጎቿ በስርዓት ትምህርቷ ላይ አካታ በማስተማር ላይ ትገኛለች፡፡
ከቻይና በተጨማሪም ሩሲያ ካሳለፍነው መስከረም ወር ጀምሮ በሞስኮ የሚገኙ አራት ትምህርት ቤቶች ውስጥ አማርኛ ቋንቋ በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡
ትምህርቱ በሳምንት ሁለት ክፍለ ጊዜ በመሰጠት ላይ መሆኑን በሞስኮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የእስያ እና አፍሪካ ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አሌክሲ ማስሎቭ በወቅቱ ተናግረው ነበር፡፡
አማርኛ ቋንቋ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የስራ ቋንቋ ሲሆን ኦሮሚኛ፣ ትግሪኛ እና ሶማሊኛ ተጨማሪ ያስራ ቋንቋዎች እንዲሆኑ ጥረቶች በመደረግ ላይ ናቸው፡፡