ሳፋሪኮም ከገበያ ኩባንያ ጋር በአጋርነት፣ እንዲሁም የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (JICA) ድጋፍ ታክሎበት “ሳፋሪኮም ታለንት ክላውድ” የተሰኘ ፕሮግራም ይፋ አድርገዋል።
ፕሮግራሙ የመረጃ መረብን በመጠቀም የሥራ ዕድልን የሚፈጥር መሆኑ ተገልጿል።
ፕሮግራሙ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነና ቀጣዩን የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች፣ ሥራ ፈጣሪዎች እንዲሁም የዲጅታሉ ዓለም መሪዎችን አቅም ለማሳደግ ያለመ ነው።
ይህ የተለየ አሠራርን ይዞ የመጣው ፕላትፎርም እስከ 2024 እ.ኤ.አ ማብቂያ ድረስ፣ ለ10 ሺሕ ልዩ ልዩ ክህሎት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች አጠቃላይ የአቅም ግንባታ እንዲሁም የሥራ ጉዟቸውን ማሳደጊያ ዕድሎችን የሚያቀርብ ነው።
ይህንን በማድረግ፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚስተዋለውን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂውን ኢንዱስትሪ ዕድገት የገታውን የቴክኖሎጂ ክህሎት እጥረት ለመቅረፍ ፕሮግራሙ ዒላማ ያደርጋል።
“የሳፋሪኮም ታለንት ክላውድ “ለመጪው ዲጂታል ዘመን የኢትዮጵያንን ሕይወት ዝግጁ ማድረግ” የሚለውን የሳፋሪኮም ተልዕኮ የሚወክል ነው” ሲሉ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና የስትራቴጂ ኦፊሰር ማሳሂሮ ሚያሺታ ያስረዳሉ።
“መጪው ጊዜ ይዟቸው ለመጣቸው ዕድሎች ያለውን ተደራሽነት ለሁሉም በማደላደል፣ አዳዲስ ነገሮችን የሚፈጥር አዲስ ትውልድ የሚነሣበትን መሠረት በመጣል ላይ እንገኛለን። ይህ ትውልድ፣ የአገሪቱን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ፣ እንዲሁም ዲጂታል ዕድገት ሞተር ሆኖ የሚያንቀሳቅስ ይሆናል። በቂ ክህሎት የጨበጡ ፕሮፌሽናሎችን ያቀፈ ማኅበረሰብ እየገነባን ነው፤ ይህ ማኅበረሰብም በመላው አገሪቱ የሚገኙትን ከቴሌኮም እስከ ፋይናንስ አቅርቦት እና ሌሎችም ኢንዱስትሪዎችን መሪ ሆኖ ለማንቀሳቀስ ዝግጁ የሚሆን ነው” ሲሉም ያብራራሉ።
የሳፋሪኮም ታለንት ክላውድ ማእከላዊ አድርጎ የያዘው የእድገቱ “ሞተር” ከጫፍ ጫፍ ያለውን የችሎታ ፍላጎት ማገናኘትን ሲሆን፣ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸውን ክህሎቶች የሚያስጨብጥ፣ የሥራ ሕይወት ጉዞ ላይ ምልከታ የሚሰጥ፣ እንዲሁም በሳፋሪኮም ሰፊ የአጋሮች መረብ ውስጥ የሚገኙ ዕድሎችን ለመጠቀም የሚያስችል ሁነኛ ድጋፍ የሚያቀርብ ነው።
የታለንት ክላውድ መፍትሔዎችን ሥራ ላይ በማዋል የተመሰከረለትን የገበያ ኩባንያን ችሎታ በመጠቀም፣ Safaricom.gebeya.com የተሟላ አገልግሎት የሚያቀርብ ይሆናል።
አገልግሎቱ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ (AI) የሚጠቀመውንና እንደ ሁኔታው ተስማሚ በሆነ መልኩ ሥራ ላይ ሊውል የሚችለውን ሶፍትዌርን እንደ አገልግሎት የሚያቀርበውን (SaaS) ፕላትፎርም በመጠቀም፣ የላቀ የቴክኖሎጂ ችሎታን አንጥሮ በማውጣት እንደየ ድርጅቱ ፍላጎት ተስማሚ መፍትሔን የሚያቀርብ ነው።
ይህን የመሰለው አገልግሎት ለበርካታ ስመ ጥር የዓለም ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችና የፎርቹን 500 (Fortune 500) ኩባንያዎች ተስማሚ ሥነ ምህዳር የፈጠረ ነው።
ሳፋሪኮም፣ ገበያ ኩባንያ እና የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ አብረው ሲሠሩ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።
በመጋቢት ወር 2016 ዓ.ም እነዚሁ አጋር ተቋማት 50 የተመረጡ ችሎታ ያላቸውን ሠራተኞች መልምለው በጋራ “ሳፋሪኮም አካዳሚን” መሥርተዋል።
ሳፋሪኮም አካዳሚ የስድስት ወር ፈጣን የሶፍትዌር ዴቨሎፕመንት ሥልጠና ፕሮግራም ሲሆን፣ የሞባይል፣ የ “ባክ ኢንድ” (Back-end) እንዲሁም “ዴቭ ኦፕስ” (DevOps) ምህንድስና ላይ፣ እንዲሁም የጀማሪ ደረጃ “ባክ ኢንድ” ሶፍትዌር ዴቨሎፕመንት ላይ ክህሎት የሚያስጨብጥ ነው።
“የሳፋሪኮም ታለንት ክላውድ ቀጣዩን የኢትዮጵያ ትውልድ ለመጪው ጊዜ ብቁ አድርጎ የሚያዘጋጅ ነው፡፡ ትውልዱን በአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ፣ በዳታ ሳይንስ፣ እና በመረጃ መረብ ደኅንነት ክህሎቶች እያስታጠቅን ነው፤ እነዚህ ደግሞ መጪውን ጊዜ የሚወስኑት ወሳኝ ቴክኖሎጂዎች ናቸው። ገበያ ኩባንያ ከሳፋሪኮም ጋር ያካሄደው ያለፈው ዓመት የተጀመረው የመጀመሪያ ዙር የሥልጠና ፕሮግራም፣ በሺሕዎች የሚቆጠሩ አመልካቾችን ያስተናገደና ምን ያህል ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለ የታየበት ነበር። ከዚህ የተነሣ የበለጠ ቁጥር ላላቸው ተደራሾች ማቅረባችን አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም” ሲሉ ከገበያ ኩባንያ መሥራቾች አንዱ እና የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አማዱ ሳፌ ይገልጻሉ።
“እዚህ ገበያ ኩባንያ ውስጥ እንደምንለው ወደዚህ ‘የታለንት ክላውድ ዘመን’ ስንገባ፣ እንዲሁ ችሎታን እያዳበርን ብቻ አይደለም። ግባችን ልዩ ልዩ ዕድሎች የሚታዩበት አመለካከት ላይ ለውጥ ለማምጣት ነው። እነዚሁን ብርቱ ቴክኖሎጂዎች ይዘው በመጠቀም የሰውን አቅም የሚያወጡ፣ እንዲሁም በመላ አህጉሪቱ እውነተና እድገትን የሚያንቀሳቅሱ አዲስ የፈጠራ ትውልድን እየገነባን ነው። የሳፋሪኮም ታለንት ክላውድ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ባለሙያዎች ፊት ቀዳሚ በመሆን ኢትዮጵያ የተጋረጡባትን ተግዳሮቶች የሚቀርፉ መፍትሔዎችን የሚያቀርቡ ይሆናሉ፤ እንዲሁም አገሪቱ ከዚህ ቀደም አይታ የማታውቀውን ዓይነት ጠንካራ የዲጂታል ኢኮኖሚ በመፍጠር ውስጥ የራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ።”
በዚህ አዲስ ፕላትፎርም፣ ገበያ ኩባንያ 38 በየዘርፉ ባለሙያዎች የተዘጋጁ ኮርሶችን የሚያዘጋጅ ሲሆን፣ እነዚህ ኮርሶችም አምስት ዋና ዋና ዘርፎችን በመያዝ በሶፍትዌር ዴቨሎፕመንት፣ መሠረተ ልማት፣ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና ዳታ፣ የዳታ ደኅንነት፣ ፕሮጀክት ማኔጅመንት እንዲሁም ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኩራሉ።
በተጨማሪም፣ በ2024 እ.ኤ.አ ገበያ ኩባንያ በኦንላይን የቴክኖሎጂ ትምህርት ዓለም አቀፍ መሪ ከሆነው ፕሉራልሳይት (Pluralsight) ጋር ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት አጋርነት ተፈራርሟል። የሳፋሪኮም ታለንት ክላውድ አባላት ሁሉ፣
ፕሉራልሳይት ባለው የጠለቀ የክህሎት ማዳበሪያ ፕላትፎርም ላይ የሚገኙ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰፊ የኮርስ አጋዥ ግብዓቶችን ያገኛሉ። ዘመን አመጣሽ የፕሮግራሚንግ ቋንቋዎችን መማሪያ ሁነኛ መንገዶች ለክላውድ መሠረተ ልማት፣ የመረጃ ደኅንነት ዘዴዎች፣ እንዲሁም “የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስና ማሽን ለርኒንግ” (AI/ML) እንዴት እንደሚውሉ ያያሉ። በዚህም የፕሮግራሙ ተሳታፊ ባለሙያዎች የፕሉራልሳይትን የተመሰከረለት የመልቲሚዲያ የመማሪያ ዘዴ በመጠቀም በየትኛውም የቴክኖሎጂ ዘርፍ መካን ይችላሉ።
የታለንት ክላውዱ አባል መሆን ከላይ ከተዘረዘሩት በተጨማሪ፣ እውቅና ባላቸው የኢንዱስትሪው ባለሙያዎች የሚመሩ የቡድን ተከታትሎ ማሠልጠኛ ክፍለ ጊዜዎች የመሳተፍ፣ ከሳፋሪኮም ለታለንት ክላውዱ አባላት ብቻ የቀረቡ ልዩ ጥቅሞችን የማግኘት፣ እንዲሁም በአፋጣኝ ክህሎትንና ፕሮፌሽናል ተመራጭነትን ለማሳደግ ታልመው የሚዘጋጁ ፈጣን የሥልጠና ፕሮግራሞች (ቡትካምፕ) ውስጥ ለመሳተፍ የመወዳደር ዕድልን ያስገኛል። ከዚህም በላይ፣ የታለንት ክላውድ አባላት ከሳፋሪኮም ተጨማሪ ጥቅሞችን ያገኛሉ፤ ከእነዚሁም አንዱ በየወሩ የ6 ጊጋ ባይት ዳታ ማግኘት ሲሆን፣ ፕላትፎርሙን ሲጠቀሙ ሊያወጡ የሚችሉትን የኢንተርኔት ወጭ ይቀንስላቸዋል። ሌላው ፕላትፎርሙን ምቹ የሚያደርገው፣ በዓመት 99 ዶላር ያህል ብቻ በኢትዮጵያ ብር በመክፈል ፕላትፎርሙን መጠቀም የሚቻል መሆኑ ሲሆን፣ ይህም ከኢኮኖሚ ሥርዓት የተነሣ የሚመጣ ፈተናን የሚያቀል የሚያስወግድ ነው።
የሳፋሪኮም ታለንት ክላውድ ዲጂታል ክህሎቶችን ለማሳደግ ይዞ የተነሣቸው ዓላማዎች በመላው ኢትዮጵያ በተቻለ መጠን ለሁሉም ተደራሽ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ሁሉም አጋሮች ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ንቁ በሆነው የኢትዮጵያ አካዳሚያዊ ሥነ ምህዳር ውስጥ ተደራሽነቱን በማስፋት፣ ይህ ተነሣሽነት እስካሁን በአገሪቱ በሚገኙ ክልሎች ውስጥ ከሚገኙ ዋና ዋና ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ስልታዊ አጋርነትን ፈጥሯል።
ከዚህ በተጨማሪ፣ የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ተጎጂ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለማገዝ በማሰብ፣ የፕሮግራሙ ተሳታፊነትን ወጪ መደጎሚያ የሚሆን ቀላል የማይባል ገንዘብ መድቧል። ይህንን በማድረግም ፕሮግራሙ ለሁሉም በእኩል መጠን ተደራሽ ሆኖ ዒላማውን እንዲመታ ታስቧል።
“የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ የኢትዮጵያን ዲጂታል ለውጥ ጉዞ ለማፋጠን የሰው አቅም ግንባታ ወሳኝ ነው” ይላሉ – የኤጀንሲው የኢትዮጵያ ዋና ተወካይ ሞሪሃራ ካትሱኪ።
“የሳፋሪኮም ታለንት ክላውድ አገራዊ ተግዳሮቶችን በሚገባ ለመቅረፍ የሚያስችሉ መሣሪያዎችን ብሩሕ ለሆኑት ኢትዮጵያውያን ከማስጨበጡ በተጨማሪ፣ አራተኛውን የኢንዱስትሪ አብዮት በአዲስ አበባ ለማስነሣትም አቅም ያለው ነው። የበለጠ ክህሎትን የጨበጠ የሥራ ማኅበረሰብ እና ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል መሠረትን በመጣል ውስጥ ድጋፍ ማድረግ በመቻላችን ኩራት ይሰማናል” ብለዋል፡፡
ታለንት ክላውዱ ከዛሬ ጀምሮ ምዝገባ ለመቀበል ክፍት የሚደረግ ሲሆን፣ ለመላው የኢትዮጵያ ትውልድ ዲጂታል አቅምን መገንቢያ ዕድል የሚያቀርብ ይሆናል።