አውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ላይ የጣለውን የቪዛ ገደብ እንዲያነሳ ተጠየቀ

የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ባሳለፍነው ሰኞ ዕለት ለኢትዮጵያውያን ዜጎች ቪዛ የመስጠት ሂደት ላይ ጊዜያዊ ገደቦች ማስቀመጡን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ህብረቱ ውሳነውን ያሳለፈው የኢትዮጵያ መንግስት በአውሮፓ ህጋዊ መኖሪያ ያላገኙ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ተባባሪ አልሆነም በሚል የቪዛ ገደብ ጥያለሁ ብሏል፡፡

በህብረቱ አዲስ ውሳኔ መሰረትም ኢትዮጵያዊያን ከዚህ በፊት ወደ አውሮፓ ሀገራት በ15 ቀናት ውስጥ ለቪዛ ጥያቄቸው ምላሽ ያገኙ የነበረ ሲሆን በአዲሱ ውሳኔ መሰረት ይህንን ወደ 45 ቀናት ከፍ አድርጓል፡፡

ውሳኔው የአገልግሎት እና ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት የያዙ የቪዛ አመልካች ኢትዮጵያዊያንንም እንደሚጨምር በወቅቱ ተገልጾ ነበር፡፡

በአውሮፓ ህብረት ዋና ከተማ ብራስልስ ያለው የኢትዮጵያ ኢምባሲ በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ የአውሮፓ ህብረት ውሳኔ የሚያበሳጭ ነው ብሏል፡፡

ኢምባሲው በመግለጫው የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያዊያን ላይ ያስተላለፈው የቪዛ ገደብ ወቅቱን ያላገናዘበ ነው ያለ ሲሆን ኢትዮጵያ በአውሮፓ ሀገራት የመኖሪያ ፈቃድ ያላገኙ ኢትዮጵያዊያንን ለመመለስ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገች ባለበት ወቅት ውሳኔው መተላለፉ ቅር እንዳሰኘውም አስታውቋል፡፡

በአውሮፓ ያለ መኖሪያ ፈቃድ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ዜግነት እና ተያያዥ መረጃዎች እየተጣሩ ነበር ያለው ኢምባሲው እነዚህን ዜጎች ክብራቸውን በጠበቀ መልኩ እንዴት መመለስ እንደሚቻል ዝግጅት እያደረግን ነበር እንጂ ተባባሪ አልነበርም ሲል ኢምባሲው በመግለጫው ላይ ጠቅሷል፡፡

የአውሮፓ ምክር ቤት ውሳኔ ኢትዮጵያ በአውሮፓ ሀገራት የመኖሪያ ፈቃድ ያላገኙ ዜጎቿን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እያደረገችው ያለውን ጥረት ሊያስተጓጉል እንደሚችልም ኢምባሲው በሰጠው ምላሽ ላይ አስታውቋል፡፡

እንዲሁም የምክር ቤቱ ውሳኔ የኢትዮጵያን እና አውሮፓ ህብረትን የረጅም ጊዜ ግንኙነትን ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው ያለው ኢምባሲው ያሳለፈውን ውሳኔ ዳግም እንዲያጤነውም ጥሪ አቅርቧል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *