በአፍሪካ በየአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በየ ዓመቱ 250 ሺህ ሰዎች ሊሞቱ እንደሚችሉ ተገለጸ

የፓን አፍሪካ አየር ንብረት ፍትህ ጥምረት ከዓለም ጤና ድርጅት ፣ አፍሪካ ጤና እና ጥናት ፋውንዴሽን፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና  ሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳቶች ዙሪያ በአዲስ አበባ የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል፡፡

በዚህ መድረክ ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ባለሙያዎች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች እና የተለያዩ ተቋማት አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

የፓን አፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ፍትህ ጥምረት ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሚቲካ ምዌንዳ በመድረኩ ላይ እንዳሉት የአየር ንብረት ለውጥ ዜጎችን ለተደራራቢ የጤና ችግሮች እየዳረገ ነው ብለዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ የሰው ልጆች ለአየር ወለድ፣ ውሃ ወለድ፣ ለምግብ እጥረት እና ሌሎች የጤና ችግሮች እየዳረገ ነው ያሉት ስራ አስፈጻሚው ጉዳቱን ለመቀነስ የተቀናጀ ስራ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው ሪፖርት የአየር ንብረት ለውጥ ቶሎ እልባት ካልተበጀለት በዓመት 250 ሺህ ሰዎችን ህይወት ሊገድል እንደሚችል አስታውቋል፡፡

እንደ ድርጅቱ ጥናት ከሆነ በአፍሪካ ከ2030 እስከ 2050 ድረስ ባሉት ዓመታት ውስጥ በየዓመቱ የሚሞቱ ዜጎችን ቁጥር ለመቀነስ አሳታፊ እና ሁሉን ያማከለ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳትን መቀነስ ይገባልም ተብሏል፡፡

የአፍሪካ ጤና እና ጥናት ፋውንዴሽን ወይም አምሬፍ የትብብር እና ውጪ ግንኙነት ዳይሬክተር ደስታ ላቀው በበኩላቸው አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ በሚያደርሳቸው ጉዳቶች ምክንያት ለውስብስብ ችግሮች እየተዳረገች መሆኗን ተናግረዋል፡፡

ዳይሬክተሯ አክለውም የአፍሪካ አባቶች እና እናቶች ከተፈጥሮ ጋር ልዩ ቁርኝት እንዳላቸው ገልጸው የምርምር ስራዎች የሀገር በቀል እውቀቶችን መሰረት ባደረገ እና ህዝቡን አሳታፊ በሆነ መንገድ ከተሰሩ ለውጥ ይመጣል ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት የተሰሩ የአየር ንብረት ለውጥ ጥናት እና ምርምር ስራዎች ውጤታማ ያልሆኑት በሌሎች ሀገራት የተሰሩ የጥናት ውጤቶችን ወደ አፍሪካ በማምጣት ቢተገበሩም ውጤታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል ያሉት ዳይሬክተሯ ለአፍሪካ ችግሮች የሚያስፈልጉት ገበሬዎችን ያማከለ እና የሀገር በቀል እውቀቶችንም ያሳተፈ ጥናት እና ምርምሮች እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡

በዓለም ጤና ድርጅት የጤና እና አካባቢ ጥበቃ ባለሙያ የሆኑት ወልተጂ ተርፋ በበኩላቸው የአየር ንብረት ለውጥ ለሰው ልጆች የጤና ቀውስ መባባስ ዋነኛ ምክንት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ባለሙያው ገለጻ የአየር ንብረት ለውጥ በሁሉም የሰው ልጆች ጤና ላይ ጉዳት እያደረሰ ቢሆንም በተለይም ሴቶችን፣ ልጃገረዶችን እና አናሳ ማህበረሰቦች ላይ የከፋ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ እነዚህ የበለጠ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ከከፋ የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል ከጉዳት ማገገም የሚችሉበት እና መላመድ የሚችሉባቸውን አሰራሮች በመዘርጋት መደገፍ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት በየጊዜው እየጨመረ የመጣ ሲሆን በ2023 ዓመት ብቻ 12 ሺህ ዜጎች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በተከሰተ ጎርፍ፣ የውሃ መጥለቅለቅ፣ ሰደድ እሳት እና የመሬት መደርመስ አደጋዎች ምክንያት ህይወታቸውን እንዳጡ የዓለም ህጻናት አድን ድርጅት ሪፖርት ያስረዳል፡፡

በዚሁ ዓመት 240 የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች የተመዘገቡ ሲሆን ይህም ከዚህ በፊት ከነበሩ አደጋዎች ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ አሁን ባለበት ጉዳት ከቀጠለ በ2050 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ህዝብ ከመኖሪያ ቤቱ ይፈናቀላል የተባለ ሲሆን ይህም ከቻይና እና ሕንድ በመቀጠል ሶስተኛው የህዝብ ብዛት እንደሚሆን የተመድ ሪፖርት ያስረዳል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *