በኢትዮጵያ 9 ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ መሆናቸው ተገለጸ

በኢትዮጵያ በፀጥታ ችግር ምክንያት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች 8.8 ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

በኢትዮጵያ በግጭት ምክንያት 8,977 ትምህርት ቤቶች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 6,483 ሙሉ በሙሉ ዝግ መሆናቸውን በሚኒስቴሩ ‘ትምህርትን በአደጋ ማስቀጠል’ ባለሙያ ንጋቱ አበበ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴሩ እና የክልል ትምህርት ቢሮዎች በጋራ በመሆን የመማር ማስተማር ሒደቱን ለማስቀጠል ጥረት ቢያደርጉም፤ አሁንም በተለያዩ ቦታዎች በቀጠሉት ግጭቶች ምክንያት ችግሩን ለመፍታት አስቸጋሪ እንደሆነ ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡

የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ የመማር ማስተማር ሒደቱን ለማስቀጠል የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉም ባለሙያው ጥሪ አቅርበዋል።

ከሚያዝያ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል ጦርነት እየተካሄደ ባለበት የአማራ ክልል ውስጥ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ መሆናቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ እንዳሉት በጦርነቱ ምክንያት ከ1 ሺህ 200 በላይ በኾኑ ኢንዱስትሪዎች ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩ ከስድስት ሺሕ በላይ ሠራተኞች ከሥራ ገበታ ውጭ ሆነዋል ብለዋል፡፡

የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊና የኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በዚህ ጦርነት ዙሪያ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በክልሉ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ከ15 ቢሊዮን በላይ ብር የሚያወጣ ንብረት ወድሟል ብለዋል፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በሰጡት መግለጫ በክልሉ በተከሰተዉ ጦርነት 298 ትምህርት ቤቶች በከፊል እና ሙሉ በሙሉ ወድመዋል ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ተማሪዎች በጦርነቱ ምክንያት ከትምህርት ውጪ ሲሆኑ 3725 ትምህርት ቤቶች ደግሞ እንደተዘጉ ሃላፊዋ ተናግረዋል፡፡

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአማራ ክልል መናገሻ ባህር ዳር ንጹሃንን ከህግ አግባብ ውጪ ገድሏል ሲል ከሷል፡፡

ድርጅቱ በሪፖርቱ እክሎም በባህር ዳር ከተማ ውስጥ አቡነ ሃራ፣ ልደታ እና ሳባ ታሚት በተባሉ አካባቢዎች ከ17 በላይ ንጹሃን በመከላከያ ተተኩሶባቸው መገደላቸውን ከአይን እማኞች ማረጋገጡን እና ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸው ሰዎች ሟቾቹን ለመቅበር እንኳን እንዳልተፈቀደላቸው አብራርቷል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም ከሁለት ወር በፊት የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት መራዊ ከተማ ከ45 በላይ ንጹሃንን ተኩሰው እንደገደሉ በባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡

አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በመራዊ ከተማ የተፈጸመው የንጹሃን ግድያ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ያሳሰቡ ቢሆንም የፌደራል መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ በሰጠው ምላሽ መከላከያ ሰራዊት የወሰደው እርምጃ ራሱን ለመከላከል ሲል እንደሆነ እና ጉዳዩም በገለልተኛ ወገን ምርመራ እንደማይደረግ አስታውቋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *