በኢትዮጵያ ካሉ የንግድ ባንኮች መካከል አንጋፋ እና ሀብታም የሆነው የንግድ ባንክ ብድር መስጠቱን አቁሟል፡፡
ንግድ ባንኩ ብድር ለማግኘት የተለያዩ ሂደቶችን አልፈው ፤ ብድሩ ተፈቅዶላቸው የመልቀቅ ሂደት ላይ ያሉትም እንዲቆም ማዘዙ ተገልጿል፡፡
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የባንኩ ደንበኛ ለኢትዮ ነጋሪ እንዳሉት የንግድ ባንክ ብድር ተፈቅዶልኝ ገንዘቡን ለመረከብ በመጠባበቅ ላይ እያለሁ ብድሩ ለጊዜው እንዲቆም መወሰኑ ተነግሮኛል ብለዋል፡፡
ሌላኛው የባንኩ ደንበኛ በበኩሉ ሶስት ሚሊዮን ብር ብድር ለመውሰድ አስፈላጊውን መስፈርቶች ሁሉ አሟልቼ ብሩ እንዲለቀቅልኝ እየተጠባበቅሁ እያለ የቅርንጫፉ ስራ አስኪጅ ደውለው ብድሩ መታገዱን ነገሩኝ ሲልም ነግሮናል፡፡
ባንኩ ብድር እንዲቆም ትእዛዝ ያስተላለፈው ከመጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ/ም ጀምሮ ነውም ተብሏል፡፡
ንግድ ባንኩ በጊዜያዊነት ብድር መልቀቅ ከማቆሙ በስተቀር ባስተላለፈው ትእዛዝ ላይ ብድር መልቀቅ ያቆመበትን ምክንያት በግልጽ እስካሁን በይፋ አልገለጸም።
ሙሉ ለሙሉ በመንግስት የተያዘው ይህ የንግድ ባንክ በኢትዮጵያ ውስጥ እስከ ዛሬ የሰጠው ብድርም ሆነ የሰበሰበው ቁጠባ ከአንድ ትሪሊየን ብር ያለፈ ብቸኛ ባንክ ያደርገዋል።
ባንኩ በቅርቡ በተገበረው የሲስተም ማሻሻያ ሳቢያ በተፈጠረ ስህተት 801 ሚሊየን ብር እንደተመዘበረበት መግለጹ ይታወሳል፡፡
በሲስተም መበላሸት ምክንያት ከተመዘበረው ገንዘብ ውስጥ አብዛኛውን ገንዘብ ማስመለሱን የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ባሳለፍነው ሳምንት በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረው ነበር።
ባንኩ ገንዘቡን የማስመለስ አካል ነው ያለውን ባልተገባ የገንዘብ ዝውውር ውስጥ ተሳትፈዋል ያላቸውን ደንበኞች ፎቶ በሁሉም ቅርንጫፎች እየለጠፈ ይገኛል፡፡
ባንኩ አሁን በጊዜያዊነት ካስተላለፈው የብድር መልቀቅ ማቆሙ ከዚህ ጋር ግንኙነት እንዳለው እና እንደሌለው እስካሁን አልተወቀም፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፈው አመት ብቻ 151 ቢሊየን ብር ብድር ሲሰጥ 165 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ደግሞ በቁጠባ መልክ መሰብሰቡን በዓመታዊ ሪፖርቱ አስታውቆ ነበር፡፡
ሆኖም ይህ በጀት አመት ከገባ ግን የቁጠባ አሰባሰቡ ከእቅዱ ጋር እየሄደ አለመሆኑ ተሰምቷል ። ለአብነትም በዚህ በጀት አመት የመጀመርያ ስድስት ወራት የሰበሰበው ቁጠባ ከእቅዱ አንጻር ከግማሽ በታች መሆኑም ተዘግቧል።
ለዚህ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ያለው የጸጥታ እና ጦርነት ችግሮች ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ባንኩ አሁን ላይ የወሰነው የብድር መልቀቅ ማቆም ውሳኔ ከጸጥታ ጋር በተገናኘ ተገቢውን ገንዘብ ከቁጠባ እና ከብድር አገልግሎቶች መሰብሰብ ባለመቻሉ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኢትዮጵያ ካሉ ባንኮች ውስጥ በሀብት መጠኑ ግዙፉ ሲሆን በመላው ሀገሪቱ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው።
የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ሀብት ከአንድ ትሪሊዮን በላይ ብር ወይም ከ18.5 ቢሊዮን በላይ ዶላር መድረሱን የባንኩ ፕሬዝዳንት ተናግረዋል።