ከመልቲቾይዝ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው ዲኤስቲቪ ለኢትዮጵያ ተመልካቾች የተለያዩ መዝናኛ ፕሮግራሞችን በማቅረብ ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ድርጅቱ በትናንትናው ዕለት ባዘጋጀው ፕሮግራም ከዚህ በፊት የነበሩ እና በቀጣይ ስለሚጀመሩ አዳዲስ የመዝናኛ ፕሮግራሞቹን አስተዋውቋል፡፡
በመድረኩ ላይ አንጋፋ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ተጽዕኖፈጣሪ ሰዎች፣ ጋዜጠኞች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
የመልቲቾይዝ ኢትዮጵያ ቁጥጥር እና ኮርፖሬት ሃላፊ አቶ መታሰቢያ በላይነህ በመድረኩ ላይ እንዳሉት መልቲቾይዝ ኢትዮጵያ ለደንበኞቹ በየጊዜው አዳዲስ የመዝናኛ ፕሮግራም እና ይዘቶችን ያቀርባል ብለዋል፡፡
ድርጅቱ በዚህ ወቅት እንዳለው ከዚህ በፊት ለኢትዮጵያ ተመልካቾች ሲያቀርባቸው ከነበሩት የመዝናኛ ፕሮግራሞች በተጨማሪ አዳዲስ ይዘቶችን እንደሚያቀርብ ገልጿል፡፡
በድርጅቱ በኩል ለኢትዮጵያ ተመልካቾች ይቀርቡ ከነበሩት ይዘቶች በተጨማሪ አዳዲስ ፕሮግራሞችን በአማርኛ እና በኦሮሚኛ ቋንቋዎች የሚተላለፉ ይዘቶች ተዋውቀዋል፡፡
ዲኤስቲቪ አሁን ላይ በአቦል ቲቪ እና አቦል ዱካ ፕሮግራሙ አፋፍ፣ አጋሮቹ፣ አቦል ሚሊየነር፣የባስሊቆስ እምባ፣ ዳግማዊ፣ ቁጭት፣ ጊዜ እና ሌሎችም መዝናኛዎች በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡
ከዚህ በፊት ሲተላለፉ ከነበሩ የመዝናኛ ይዘቶች በተጨማሪም ሰዋሰው፣ የውሃ ሽታ፣ አብሱማ፣ አንድ እድል፣ የእግዜር ያለ፣ እሹሩሩ፣ እንቁጣጣሽ እና ሌሎችም በቅርቡ ለተመልካቾች መተላለፍ የጀመሩ መዝናኛዎች ናቸው፡፡
በአፋፍ ፊልም ላይ በዋና ገጸ ባህሪ የምትተውነው አርቲስት መዓዛ ታከለ በመድረኩ ላይ ባደረገችው ንግግር መልቲቾይዝ ኢትዮጵያ ህልማችንን እንድንኖር ረድቶናል ብላለች፡፡
የጥበብ ሙያ ፣ ተሰጥኦ እና ፍቅር እያለን በገንዘብ እና ሌሎች ችግሮች ምክንያት የኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ተጎድቶ ነበር የምትለው አርቲስቷ መልቲቾይዝ የጎደለንን እድል ይዞል መጥቷል ስትልም አክላለች፡፡
መልቲቾይዝ ባ2022 ዓመት ብቻ በአፍሪካ በ40 ቋንቋዎች ከ6 ሺህ በላይ ሰዓት ይዘቶችን በ50 ሀገራት አቅርቧል የተባለ ሲሆን በየቀኑ ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ተመልካች አለውም ተብሏል፡፡
መልቲቾይዝ ኩባንያ በአሁኑ ሰዓት ከ21 ሚሊዮን በላይ ሰብስክራይበር ያለው ሲሆን በአፍሪካ ቀዳሚ የመዝናኛ ፕሮግራምም ነው፡፡