ንግድ ባንክ ባሳለፍነዉ አርብ መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም ሌሊት ባጋጠመዉ ችግር 25 ሺ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር መደረጉና 2.6 ቢሊየን ብር መንቀሳቀሱን አስታውቋል
ባንኩ ገንዘብ የወሰዱ ሰዎችን ለመጠየቅና ገንዘቡን ለማስመለስ ግብረሀይል ያቋቋመ ሲሆን በባንኩ ዲጂታል መዋቅር ላይ በውስጥ አዋቂ የተፈፀመ ጥቃት ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ገምተዋል፡፡
ቅዳሜ ዕለት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዲጂታል መዋቅር ላይ የተከሰተውን ግድፈት ተጠቅመው ገንዘብ የወሰዱ አካላትን ለማደን ግብረ ኀይል መቋቋሙ ተገልጿል፡፡
ግብረ ሀይሉ ከብሔራዊ ባንክና ከንግድ ባንክ ባለሙያዎች እንዲሁም ከፀጥታ አካላት የተካተቱበት ነው የተባለ ሲሆን ዓላማው ደግሞ በስድስት ሰዓታት ጊዜ ውስጥ ከባንኩ ያለ አግባብ የተወሰደውን ገንዘብ ማስመለስ እና ማጣራት ነው፡፡
ይሁንና ባንኩ በተባለው ሰዓታት ውስጥ የተወሰደበትን የገንዘብ መጠን ያላሳወቀ ሲሆን ፎርቹን ጋዜጣ እንደዘገበው ግን ከ66 ሺህ በላይ ደንበኞች አካውንት በችግሩ ተስተጓጉሏል ተብሏል፡፡
አርብ ለቅዳሜ ሌሊት ለስድስት ሰዓታት በቆየው የአገልግሎት መስተጓጎል 25 ሺ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር መደረጉን እንዲሁም 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ተንቀሳቅሷል የተባለ ሲሆን ባንኩ መረጃውን ማረጋገጥ እንዳልፈለገ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
አንዳንድ የትምህርት ተቋማት ከወዲሁ ገንዘብ ከኤቲኤም ማሽኖች የወሰዱና በህገወጥ ዝውውሩ የተሳተፉ ተማሪዎች ገንዘቡን ለባንኩ እንዲመልሱና ራሳቸውን ከህግ ተጠየቂነት እንዲያተርፉ የሚያሳስብ ጥሪ ተላልፎላቸዋል፡፡
ንግድ ባንክ ላይ የደረሰው ችግር የሳይበር ጥቃት አለመሆኑንና ነግር ግን የተቋሙ ውስጣዊ ግድፈት መሆኑን ባወጣው ተደጋጋሚ መግለጫ ገልጿል።
ዋዜማ ሬዲዮ የውስጥ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው የንግድ ባንክ እንዳሉት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ዕለት 100 ሚሊዮን ብር አንድ መንግስታዊ የባንክ ክፍያ ከአንድ በላይ የከፋይ ወገን በዲጂታል ፊርማ ሊያፀድቀው ሲገባ በአንድ ሰው ፈራሚነት ወደ ተከፋይ መተላለፉን የባንኩን ሀላፊዎች አስደንግጦ ነበር ተብሏል።
ባንኩ አርብ ዕለት ይህንን ተገቢውን የክፍያ ሂደት ሳይጠብቅ ተከፈለ የተባለውን የ100 ሚሊዮን ብር ክፍያን ለማጣራት ችግሩን ለማወቅና ለመፍታት ሙከራ ሲደረግ መዋሉን ነገር ግን ሌሊት ላይ ይህ የከፋ ቀውስ ሊከሰት እንደቻለም ተገልጿል፡፡
ባንኩ የሳይበር ጥቃት እንዳልተፈጸመበት ይናገር እንጂ ክስተቱ በባንኩ ዲጂታል መዋቅር ላይ በውስጥ አዋቂ የተፈፀመ ጥቃት ሊሆን እንደሚችል የሳይበር ደህንነት ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ባንኩ ከተጭበረበረ የትምህርት ማስረጃ ጋር በተያያዘ ከ200 በላይ ሰራተኞችን ባሳለፍነው ሳምንት ከስራ ማሰናበቱ ይታወሳል፡፡
ብሔራዊ ባንክ በበኩሉ ቅዳሜ እለት በንግድ ባንክ ላይ ያጋጠመው የአገልግሎት መቋረጥ በባንኩ አገልግሎት መስጫ ሥርዓት ላይ ከተደረገ የደኅንነት ፍተሻና የማሻሻያ ሥራ ጋር የተያያዘ እንደኾነ ገልጧል።
ብሄራዊ ባንክ፣ ክስተቱ የባንኩን፣ የደንበኞቹንና አጠቃላይ የፋይናንስ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል አለመኾኑን አረጋግጫለኹም ብሏል።
ባንኩ፣ ችግሩ ባስከተላቸው ጉዳቶች ላይ ምርመራ አድርጎ ውጤቱን ወደፊት እንደሚገልጥ ያስታወቀ ሲሆን ባኹኑ ወቅት የኹሉም የፋይናንስ ተቋማት የፋይናንስ ሥርዓቶች ደኅንነቸው የተጠበቀ መኾኑን ባንኩ ገልጦ፣ ኅብረተሰቡ ያለ ስጋት የፋይናንስ አገልግሎቶችን መጠቀም እንዲቀጥል አሳስቧል።