ከ800 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ወደ ውጭ ሀገራት መሰደዳቸው ተገለጸ

ባለፉት አምስት ዓመታት ከ800 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ወደ ውጭ ሀገራት ፈልሰዋል የተባለ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 78 በመቶ የሚሆኑት ወጣት ከመሆናቸውም በላይ አብዛኞቹ ሴቶች መሆናቸው ተነግሯል ።

የኢትዮጵያ ዜጎች በስራ ዕድል እጦት የተነሣ በተለያዩ መተላለፊያዎች ድንበር አቋርጠው እንደሚፈልሱ የተገለፀ ሲሆን ድህነት ፣ የሰላም እጦት፣ የመነሻ ሐብት ምንጭ እጥረት ፣ የአየር ንብረት መለዋወጥና የተፈጥሮ ውድመት ዋና ዋና ገፊ ምክንያቶች እንደሆኑ ተገልጿል ።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያዊያን ድንበር አቋርጠው እንዲፈልሱ ሳቢ ከሆኑ ምክንያቶች መካከል ለራሳቸውና ቤተሰባቸው ገቢ የማመንጨት  ፍላጎት መኖር እና  የተሻለ ህይወት ፍለጋ እንደሆነ ይጠቀሳሉ ተብሏል ።

የኢትዮጵያ ፍልሰተኛ ሰራተኞች ለኢትዮጵያ መልካም ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ሲሆን ሀገሪቱ ውጭ ከሚኖሩና ከሚሰሩ ዜጎቿ ዳጎስ ያለ የውጭ ምንዛሪ እንደምታገኝ ተጠቁሟል ።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ፍልሰተኛ ሰራተኞች አድላዊ ገደብና አፍሶ መመለስ የተጫነው በርካታ ጥቃቶችና የመብት ጥሰትች የተጋለጡ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት የሆኑት አ/ቶ ካሣሁን ፎሎ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በመተላለፊያዎች አደገኛ ለሆነ እንግልት እና በመድረሻ ሀገራት ጥቃትን ፣ ብዝበዛን ፣ አድልዎን ፣ የሰራተኛ መብቶች ጥሰትን ፣ የማህበራዊ ከለላ እጦትን ያካተቱ አዳጋች የስራ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል ብለዋል ።

ሆኖም ዓለም አቀፋዊ ባሕርይ ያለውን የፍልሰተኛ ሰራተኞች ሰብዓዊና የሠራተኛ መብቶች ለማስከበር ፣ ለችግሮቻቸው መፍትሄ ለመሻት እና የሕግ ከለላ ለመስጠት አግባብ ያላቸው የዓለም ስራ ድርጅት ድንጋጌዎች እጅግ አስፈላጊ መሆናቸው ተገልጿል ።

ስለሆነም ስለ ፍልሰተኛ ሰራተኞች የተደነገጉ የዓለም ስራ ድርጅት ድንጋጌ ቀጥር 97 እና 143 በማፅደቅ ለመብት ተኮርና ሕጋዊ ፍልሰት አስተዳደር እውን መሆን አስተዋጽኦ ማበርከት ይገባል ተብሏል ።

በተለይም እነዚህን ድንጋጌዎች ማፅደቅ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚሰሩ ዜጎችን ለመከላከልና ከተቀባይ ሀገራት ጋር የፍልሰተኞች መግባቢያ ሰነዶች ለመፈራረም ፣ በመነሻ ፣ በመተላፊያ እና በመዳረሻ የፍልሰተኛ ሰራተኞች መልካም አስተዳደር ለማስፈን እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ገፅታ ለመገንባት አስተዋጽኦ እንዳለው ተገልጿል ።

እንደ ዓለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት አይኤልኦ ጥናት ከሆነ 3 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ሲሆን አብዛኞቹ ግን በመካከለኛው መስራቅ ሀገራት የሚኖሩ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ውጪ ሀገራት ተሰደው ከሚኖሩ ዜጎቿ በዓመት ከአራት ቢሊዮን በላይ ዶላር ገቢ የምታገኝ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ዲያስፖራ ኢትዮጵያዊያን ገንዘባቸውን በባንክ በኩል እየላኩ ባለመሆኑ የሚገኘው የሬሚታንስ ገቢ እየቀነሰ መጥቷል፡፡

ሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬት፣ ኩዌት፣ ኳታር፣ ጆርዳን፣ አውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ ኢትዮጵያዊያን በብዛት የተሰደዱባቸው ሀገራት እንደሆኑ የአይኤልኦ ሪፖርት ያስረዳል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ባሳለፍነው ዓመት በሳውዲ አረቢያ በህገ ወጥ መንገድ ይኖሩ የነበሩ 100 ሺህ ኢትዮጵያዊያንን ከሳውዲ አረቢያ እና ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ጋር በመተባበር ወደ ሀገራችው መልሷል፡፡

ይሁንና አሁንም ከ80 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን በሳውዲ አረቢያ የተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ ታስረው እንዳሉ የተገለጸ ሲሆን ወደ ሀገራቸው እንዲመልሷቸው የኢትዮጵያን መንግስት ጠይቀዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *