ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ተቋማት ወደ ሀገሯ እንዲመጡ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና ሌሎች ተቋማት በኩል እያስተዋወቀች ትገኛለች።
በዚህም መሰረት እስካሁን 25 የዳታ ማይኒንግ ድርጅቶች የተመዘገቡ ሲሆን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ጋር የሀይል አቅርቦት ስምምነት በመፈራረም ላይ ናቸው።
ከ25ቱ ተቋማት ውስጥም አራቱ ሥራ መጀመራቸውን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የገበያና ቢዝነስ ልማት መምሪያ አስታውቋል።
የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ህይወት እሸቱ እንዳስታወቁት የዳታ ማይኒንግ ኩባንያዎቹ በሀገር ውስጥ ኃይል የሚጠቀሙ ቢሆንም የፍጆታ ሂሳባቸውን በዶላር እንዲከፍሉ ከስምምነት ተደርሷል ብለዋል፡፡
የኢንቨስትመንት ፍቃድና ሌሎች አስፈላጊ መስፈርቶችን ካሟሉት ከሃያ አምስቱ ድርጅቶች መካከል አራቱ ከ10 እስከ 100 ሜጋ ዋት ድረስ ኃይል መጠቀም ጀምረዋልም ተብሏል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገር ውስጥ በውጭ ምንዛሪ ከተከናወነው ሽያጭ አስቀድመው ሥራ ከጀመሩት ከሁለቱ የዳታ ማይኒንግ ድርጅቶች ብቻ ከሁለት ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልፀዋል።
የቀሪዎቹ ሁለት ድርጅቶች የፍጆታ ሂሳብ በቀጣዩ ወር መሰብሰብ እንደሚጀምር ነው ያስታወቁት፡፡
አቶ ህይወት እንደገለፁት በዳታ ማይኒንግ ዘርፍ ለመሰማራት ፍቃድ ከወሰዱትና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር የኃይል ሽያጭ ስምምነት ከተፈራረሙት አስራ ስምንት ድርጅቶች መካከል አምስቱ ግንባታ ሲጀምሩ አስሩ ደግሞ ግንባታ ለመጀመር በሂደት ላይ እንደሆኑ ተገልጿል።
ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት የተፈራረሙት ድርጅቶች ምናባዊ ግብይትን ማካሄድ ወይም ለዚህ የሚረዱ መረጃዎችን የሚሰጡ ናቸው።
ከሁለት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የትኛውንም የምናባዊ ገንዘብ ግብይት ወይም ክሪፕቶ ከረንሲ ግብይት እንዳልፈቀደ እና ግብይት ሲፈጽሙ የተገኙ ሰዎችም በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ አስታውቆ ነበር፡፡
ካሳለፍነው ዓመት ጀምሮ በኢትዮጵያ የቢትኮይን ግብይት መፈጸም የሚያስችሉ መሰረተ ልማት ግንባታ የሚያደርጉ ኩባያዎች ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል፡፡
ኢትዮጵያ አሁንም የክሪፕቶከረንሲ ግብይት እንዲደረግ ያልፈቀደች ሲሆን የዳታ ማዕከል ግንባታዎች እንዲካሄዱ ግን ስምምነቶችን በመፈራረም ላይ ነች፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ዌስት ዳታ ማዕከል የተሰኘው የቻይና ኩባንያ የ250 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት በአዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ጋር ተፈራርሟል፡፡
በዚህ ስምምነት መሰረት የቢትኮይን ግብይት እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ጉዳዮች ዙሪያ ስልጠና መስጠት የሚያስችሉ እንደሆኑም ተገልጿል፡፡
በዓለም ላይ ካሉ ምናባዊ የመገበያያ ገንዘብ ተቋማት መካከል ግማሽ ያህሉ በአሜሪካ ቴክሳስ የከተሙ ሲሆን በቀን በአማካኝ 2 ሺህ 300 ሜጋ ዋት ሀይል እንደሚጠቀሙ ጥናቶች ያስረዳሉ።
የነዚህ ተቋማት የሀይል ፍጆታ ዋጋ ታሪፍ ከፍተኛ መሆኑ ኩባንያዎቹ ወደ ሌሎች ሀገራት በመዛወር ላይ ናቸው ተብሏል፡፡Top of Form