የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና በራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሄ አብዲ ከሶስት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ በኤደን ባህረ ሰላጤ 20 ኪሎሜትሮች የሚረዝም የባህር ጠረፍ እንድትከራይ እና በምትኩ ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና እንድትሰጥ የሚያስችል ነው።
ይህ ስምምነት ሶማሊላንድን የራሷ ሉአላዊ ግዛት አድርጋ በምታያት ሶማሊያ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።
ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ የበረራ ቁጥሩ ET8372 የተሰኘ አውሮፕላን ወደ ራስ ገዟ ሶማሊላንድ በዛሬው ዕለት በረራ በማድረግ ላይ እያለ እንዲመለስ መደረጉ ተገልጿል፡፡
የሶማሊያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በቀድሞ ስሙ ትዊተር አሁን ኤክስ አካውንቱ ይፋ እንዳደረገው የግዛቴ አካል ናት ወደ ሚላት ሶማሊላንድ ሀርጌሳ እየበረረ የነበረ አውሮፕላን እንዳያርፍ መከልከሉን አስታውቋል፡፡
እንዲመለስ የተደረገው አውሮፕላን የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናትን ይዞ እንደነበር ብሉምበርግ በጉዳዩ ዙሪያ በተጨማሪነት ባወጣው ዘገባው ላይ ጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ራስ ገዟ ሶማሊላንድ ዋና ከተማ ሃርጌሳ ሲጓዝ የነበረው አውሮፕላን በሶማሊያ አልተፈቀደም በሚል ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ ለማረፍ መገደዱን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ከተፈራረመችበት ጊዜ አንስቶ ከሶማሊያ ጋር አለመግባባት የተከሰተ ሲሆን የአሁኑ ክስተት ደግሞ ግንኙነቱን የበለጠ እንደሚያካርረው ይጠበቃል፡፡
አሜሪካ፣ ቻይና፣ የአውሮፓ ህብረት፣ አፍሪካ ህብረት እና ሌሎችም ሀገራት የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የመግባቢያ ስምምነትን አስመልክቶ ባወጡት መግለጫ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እንደሚያከብሩ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡