የዓለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ድርድርን እና ቀጣናዊ የንግድ ትስስሮችን የሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ በአዲስ መልክ መቋቋሙን የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ኮሚቴው ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ከፍተኛ አመራሮችን እንዲሁም ባለሙያዎችን ያካተተ ነው ተብሏል።
ኢትዮጵያ የአለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በተለያዩ ጊዜያት ፍላጎቷን ብታሳይም ከአባል አገራት ለሚነሱ አንዳንድ የንግድ ዘርፍ አካታችነት አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ባለመቻሏ ድርጅቱን መቀላቀል ሳትችል ቆይታለች።
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት ከአምስት ዓመት በፊት ወደ ስልጣን ሲመጣ የዓለም ንግድን በአባልነት መቀላቀል እንደሚፈልግ በይፋ ጥያቄ አቅርቧል፡፡
መንግስት ከወሰዳቸው ስር ነቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እና አዳዲስ ለውጦች መካከል አገሪቱን በ2021 የአለም ንግድ ድርጅት አባል ማድረግ ይገኝበታል።
በዚህም ከ2020 አንስቶ ድርድር እንደ አዲስ የተጀመረ የተጀመረ ሲሆን ከዚህ ጎን ለጎንም ቀደም ሲል አባል አገራት (በተለይ አሜሪካ እና ካናዳ) ከሚያስቀምጧቸው ወሳኝ የሚባሉ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል እንደ የፋይናንስ እና ቴሌኮም ዘርፎች ለሌሎች ይከፈቱ የሚለውን ጥያቄ ምላሽ የመስጠት ስራ በመንግስት በኩል ሲሰራ ቆይቷል።
ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች በታቀደው ጊዜ ወደ አባልነት የልመጣችው ኢትዮጵያ ድርጅቱን እኤአ በ2026 ለመቀላቀል አዲስ እቅድ ማውጣቷ ተገልጿ፡፡
በቀጣዩ ማክሰኞ በይፋ የተመሰረተበትን 29ነኛ አመቱን የሚዘክረው ድርጅቱ በሚተዳደርበት ህግ መሰረት አዲስ አገር ለመቀበል የሁሉም አባል አገራት ይሁንታ የግድ ነው።
በዚህም ድርጅቱን በመቀላቀል ሂደት ውስጥ የአባል አገራት የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች እና ስጋቶች በአጥጋቢ ሁኔታ መመለስ ተገቢ በመሆኑ የድርድሩ ሂደት ፈታኝ እና ረጅም ጊዜ የሚጠይቅ መሆኑ ይጠቀሳል።
ኢትዮጵያ እኤአ ከ2003 ጀምሮ በዓለም ንግድ ድርጅት ውስጥ በታዛቢነት እየተሳተፈች ሲሆን ቋሚ አባል ለመሆን ደግሞ የንግድ ፖሊሲዎችን ከማሻሻል ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ናት፡፡
በአፍሪካ ካሉ 55 ሀገራት መካከል 26 ሀገራት የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ሲሆኑ ከምስራቅ አፍሪካ ጅቡቲ እና ኬንያ ብቻ አባል ናቸው፡፡
164 የዓለማችን ሀገራት አባል የሆኑበት የዓለም ንግድ ድርጅት 16 ሀገራት ብቻ ድርጅቱን በታዛቢነትም ሆነ በአባልነት ለመቀላቀል ፍላጎት እንደሌላቸው ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ አፍጋኒስታን፣ ላይቤሪያ፣ ሱዳን፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና የመን የዓለም ንግድ ድርጅትን በአባልነት ለመቀላቀል ጥያቄ ያቀረቡ ሀገራት ናቸው፡፡
የዓለም ንግድ ድርጅት በ1995 የተቋቋመ ሲሆን ዋና መቀመጫውም ጀኔቫ ስዊዘርላንድ በማድረግ ዓለምን ንግድ ለማቀላጠፍ ዓላማው አድርጎ እንደተቋቋመ ተገልጿል፡፡