ኢትዮጵያ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አገኘች

ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር መገኘቱ ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ ከሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በአራት ዓመታት ውስጥ ወደ ውጪ ሀገራት ከተላኩ ምርቶች አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በዓመት 17 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የሚያስገኙ የተለያዩ የፕላስቲክ ቱቦዎችን የሚያመርት ፋብሪካ ተመርቆ ሥራ ጀምሯል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አክሊሉ ታደሠ፤ ኮርፖሬሽኑ ከሚያስተዳድራቸው 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች የተለያዩ ምርቶች ለውጭ ገበያ እየቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ለተለያዩ ሀገራት ገበያ ከሚያቀርቧቸው ምርቶች በአራት ዓመታት ውስጥ አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ሀላፊው ተናግረዋል፡፡

ከውጭ ሀገራት ይገቡ የመበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት የተጀመረ ሲሆን 550 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን እንደተቻለ ሃላፊው አስረድተዋል።

በሃዋሳ፣ በድሬዳዋ፣ በባህር ዳር፣ በደብረ ብርሃን፣ በሠመራ፣ በጅማና በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች በተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የጨርቃጨርቅ፣ የግብርና ምርቶች፣ የፕላስቲክና የተለያዩ ምርቶች ለውጭ ገበያ እየቀረቡ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከውጭ ይገባ የነበረውን ምርት በሀገር ውስጥ በመተካት በተለይ በቢራ ብቅልና በተለያዩ የኢንዱስትሪ ምርቶች ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

ይሁንና በሀገሪቱ ያጋጠሙት የጸጽታ ችግሮች ለኢንዱስትሪ ፓርኮች የምርት ግብዓት እጥረት እየፈጠሩ ነውም ተብሏል፡፡

የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጉልላት አበበ በበኩላቸው ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ከገቡ ፋብሪዎች የምርት ሽያጭ ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን አስታውቀዋል።

በአዳማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ውስጥ በ14 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር የተገነባውን የፕላስቲክ ቱቦ ማምረቻ ፋብሪካ ወደ ሥራ በመግባቱ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስገኝ ገልጸዋል።

የኢዜድኤም ንግድና ኢንቨስትመንት ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ እስመለዓለም ዘውዴ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ፋብሪካው ጥራት ያላቸውን ምርቶች በወቅቱ በማቅረብ የፕላስቲክ ቱቦዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ ለመቀነስ ያስችላል፡፡

በማምረቻው አማካኝነት በአፍሪካ ውስጥ አስተማማኝና ተመራጭነት ያለው የፕላስቲክ ቱቦዎችና መገጣጠሚያዎች ማቅረብ የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል ብለዋል።

ፋብሪካው ከ200 ለሚበልጡ ሠራተኞች ቋሚ የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን በተለያዩ የንግድ ትስስርና በተለያዩ አማራጮች ለ400 ኢትዮጵያውያንም የሥራ ዕድሎችን አቅርቧል።

ከሁለት ዓመት በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ አሜሪካ የተለያዩ የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን መጣሏ ይታወሳል፡፡

ከማዕቀቦቹ ውስጥ ኢትዮጵያን ከአሜሪካ ነጻ የንግድ እድል ወይም አግዋ ማገድ አንዱ ሲሆን በዚህም ምክንያት በተለይም የኢንዱስሪ ፓርኮች በማዕቀቡ ተጎድተዋል፡፡

ምርቶቻቸውን ወደ አሜሪካ፣ አውሮፓ እና እስያ ገበያዎች ይልኩ የነበሩ ኩባንያዎች አሜሪካ ማዕቀቧን ለተጨማሪ አንድ ዓመት በማራዘሟ ወደ ሌላ ሀገር እንዲሰደዱ እያደረገ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *