ቻይና በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ልህቀት ማዕከል ለመገንባት ተስማማች

ይህ የቴክኖሎጂ ልህቀት ማዕከል ግንባታ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ይፈጃል ተብሏል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና የቻይናው ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የቴክኖሎጂ ልኅቀት ማዕከል ለመገንባት የውል ስምምነት ሠነድ ተፈራርመዋል፡፡

የልህቀት ማዕከል ግንባታው ኮተቤ በሚገኘው የተቋሙ ግቢ ውስጥ ይገነባል የተባለ ሲሆን ለፕሮጀክቱ 9 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ተመድቧል ተብሏል፡፡

ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሽፈራው ተሊላና የቻይና ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ኤክስኪዩቲቭ ማኔጅንግ ዳይሬክተር ው ጁይ ናቸው፡፡

ማዕከሉ ሲጠናቀቅ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር የተጣጣመና ለደንበኞች የሚሰጠውን አገልግሎት አስተማማኝ፣ ቀልጣፋና ዘመናዊ የሚያደርግ እንደሆነ አቶ ሽፈራው ገልጸዋል፡፡

ው ጁይን  በበኩላቸው የማዕከሉን ግንባታ በተያዘለት ጊዜ በጥራት  አጠናቅቀው እንደሚያስረክቡ አረጋግጠዋል፡፡

ማዕከሉ የኤሌክትሪካል ቴክኖሎጂ ሙያ የሰው ኃይል ማሰልጠኛ፣ የምርምርና የልኅቀት ማዕከል፣ ብሄራዊ የዲስትሪቢዩሽን ስካዳ መቆጣጠሪያ ጣቢያ፣ የዲስትሪቢዩሽን ዕቃዎች ፍተሻ እና ላቦራቶሪ ፋሲሊቲዎች ይኖሩታል፡፡

በተጨማሪም ዘመናዊ የስብሰባ አዳራሽ፣ የሰልጣኞችና እንግዶች መኝታ ቤቶች፣ ካፍቴሪያ እና ልዩ ልዩ የስፖርት መሰረተ ልማቶችን ያካተተ ነው መባሉን የኤሌክትሪክ አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡

ማዕከሉ ዘጠኝ የተለያዩ ስፋትና ከፍታ ያላቸው ሕንፃዎች፣ በፊፋ ስታንዳርድ መሰረት የእግር ኳስ ሜዳ፣ የሩጫ ትራክ፣ የግራውንድ ቴኒስ ሜዳ፣ ቮሊ ቦል፣ ሀንድ ቦል፣ ባስኬት ቦል፣ የተሟላ ጂም፣ ልዩ ልዩ የሳይት ግንባታዎች የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገዶች እና የፍሳሽ መስመሮችን ያጠቃለለ ነው ተብሏል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *