የባሌ ተራሮች እና የጌድኦ መልክዓምድር በዩኔስኮ ተመዝግበዋል።
ኢትዮጵያ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶቿን ብዛት ወደ 11 ከፍ በማድረግ ከአፍሪካ በአንደኝነት ተቀምጣለች።
የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅትወይም ዩኔስኮ 45ኛ ጉባኤውን በሳውዲ አረቢያ ሪያድ እያካሄደ ይገኛል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ጌዴኦ ዞን የሚገኘው የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር እና የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የዓለም ቅርስ ሆነው መመዝገቡ ተገልጻል።
ዩኔስኮ በድረገጹ እንዳስታወቀው የጌድኦ ባህላዊ መልከዓ ምድር እና የብርቅዬ የዱር እንስሳት መገኛ የሆነው የባሌ ብሔራዊ 10ኛ እና 11ኛ ቅርስ ሆነው መመዝገባቸውን ለዓለም አብስሯል።
ኢትዮጵያ በአጠቃላይ 11 ቅርሶችን በዩኔስኮ መዝገብ ስር በዓለም ቅርስነት ያስመዘገበች ሲሆን ከአህጉሪቱ ደቡብ አፍሪካን በመብለጥ በአንደኝነት ትመራለች።
ደቡብ አፍሪካ 10 ቅርሶችን ስታስመዘግብ ሞሮኮ ከደቡብ አፍሪካ በመቀጠል ዘጠኝ ቅርሶችን በዩኔስኮ ስታስመዘግብ ቱኒዝያ ስምንት እንዲሁም ግብጽ፣ ሴኔጋል እና ታንዛኒያ ደግሞ ሰባት ቅርሶችን ያስመዘገቡ ሀገራት ናቸው።
ኢትዮጵያ በሪያድ እየተካሄደ ባለው የዩኔስኮ ጉባኤ ላይ የቱሪዝም ሚኒስትሯ ናሲሴ ጫሊ፣ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናት ዳይሬክተር አበባው አያሌው እና ሌሎች ባለሙያዎች ተወክላለች።
በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡት የጌድኦ ባህላዊ መልከዓ ምድር እና ባሌ ብሔራዊ ፓርክ በዕጽዋዕት፣ ፍራፍሬ እና በሰብል ምርቶች ታዋቂነትን ያተረፉ የብዝሀ ህይወት ማዕከላት ናቸው።
ኢትዮጵያ ይህን ቅርስ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ላለፉት 10 ዓመት በይፋ አመልክታ ክትትል ስታደርግ እንደነበር ተገልጿል።