ኢትዮ ቴሌኮም የአምስተኛው ትውልድ (5G) የሞባይል አገልግሎትን በአዲስ አበባ በወዳጅነት አደባባይ በተካሄደ መርሃ ግብር በይፋ አስጀምሯል።
በመርሃ ግብሩም ተቋሙ ከዚህ ቀደም በቅድመ ገበያ ሙከራ ደረጃ በአዲስ አባባ እና አዳማ ከተሞች አስጀምሮት የነበረውን የ5G የሞባይል አገልግሎት፤ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ በ145 ጣቢያዎች ማስጀመሩን አብስሯል።
ይህ የ5G የሞባይል ኔትዎርክ አገልግሎት እስከ 10 ጊጋ ባይት በሰከንድ የሚደርስ ፍጥነት እንዳለው የተገለጸ ሲሆን፤ ዳታ የማስተላለፍ መዘግየትን እጅግ በላቀ ኹኔታ በመቀነስ ወደ 1 ሚሊ ሰከንድ ያደርሳል ተብላል።
የ5G አገልግሎት በተለይም በተመሳሳይ ወቅት መከናወን የሚፈልጉ እንደ የማምረቻ ፋብሪካዎች፣ ግብርና፣ ሕክምና ለመሳሰሉ ዘርፎች የላቀ ፋይዳ እንዳለውም ተገልጿል።
የ5G አገልግሎት ሥራ ላይ መዋል የማህበረሰቡን ሕይወት የሚያቀሉ ዲጂታል መፍትሄዎችን በቀላሉ በማቅረብ ተሞክሯቸውን የሚያሻሽል መሆኑን ጠቁሟል።
አገልግሎቱ ለቢዝነስ ደንበኞች ምርታማነታቸውን እና የአሠራር ቅልጥፍናቸውን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርስ መሆኑም ታምኖበታል።
የ5G የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት ለዘመናዊ ቤት፣ ለስማርት የጤና አገልግሎት እና የሆስፒታል አስተዳደር፣ ለስማርት ግብርና፣ ለትምህርት፣ ኢንዱስትሪ እና ሌሎች ወሳኝ አግልግሎቶች ከፍተኛ ፋይዳ ያለው የዘመኑ የመጨረሻ ቴክኖሎጂ ነው ተብሏል።
ሆኖም ተቋሙ አገልግሎቱን በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ለማስጀመር ለደንበኞቹ ያልተገደበ ዳታ፣ የመደበኛ የመኖሪያ ቤት እንዲሁም የተለያዩ ጥቅሎችን ማቅረቡን ገልጾ፤ “ደንበኞች ይህን አገልግሎት ለማግኘት የ5G ሞባይልን ለመጠቀም የሚያስችሉ መሳርያዎችና የሞባይል ቀፎዎች ሊኖራቸው ይገባል።” ብሏል።