በአሶሳ ዞን የወርቅ ማዕድን ማውጫ ተደርምሶ የስድስት ሰዎች ህይወት አለፈ

በአሶሳ ዞን በመንጌ ወረዳ ሸጎል ቀበሌ  አሚር ካምፕ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ተደርምሶ የስድስት ሰዎች ህይወት ማለፉን የወረዳው ፖሊስ ገልጿል።

ነሃሴ 24 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 7 ሰዓት ገደማ በአካባቢው ለወርቅ ማዕድን ማውጣት ስራ ጉድጓድ በመቆፈር ላይ ከነበሩ ዘጠኝ ግለሰቦች መካከል የስድስት ሰዎች ህይወት ማለፉን የመንጌ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አዛዥ ረዳት ኢንስፔክተር አሳድቅ አብዱልፈታህ ተናግረዋል።

ቀሪ ሶስት ሰዎች ደግሞ በአደጋው ቀላል እና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል የተባለ ሲሆን ተጎጂዎች በመንጌ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እና በአሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል ብለዋል።

በወቅቱ ግለሰቦችን በህይወት ለመታደግ በሰውና በመኪና የታገዘ ጥረት ቢደረግም ቦታው አስቸጋሪ ከመሆኑ የተነሳ መታደግ እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

ይህን መሰሉ አደጋ ከአሁን ቀደም አጋጥሞ እንደነበር የተናገሩት አዛዡ በጥንቃቄ ጉድለት የማዕድን ማውጫዎች ተደርምሰው ለሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት  መሆኑን ጠቅሰዋል።

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በማዕድናት በተለይም በወርቅ ማውጣት ከኢትዮጵያ ታዋቂ ክልል ሲሆን ለብሔራዊ ባንክ በየዓመቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ በማስገባት ቀዳሚው ነው፡፡
በክልል የነበረው አለመረጋጋት እና ህገወጥ የማዕድን አዘዋወሪዎች አማካኝነት ኢትዮጵያ ከወርቅ ማዕድን የምታገኘውን ገቢ እንዲቀንስ አድርጎ ቆይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከ20 በላይ የውጭ ሀገራት ዜጎች ከአካባው ወርቅ በህገወጥ መንገድ ሲያወጡ እና ሲያዘዋውሩ ተገኝተዋል በሚል ከሁለት ወር በፊት በቁጥጥር ስር ማዋሉ ይታወሳል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *