በአማራ ክልል በርካታ ከተሞች በሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ እየተካሄደ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በሁለቱ አካላት መካከል ውጊያ መጀመሩን ተከትሎ በአማራ ክልል የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን ከነዋሪዎች አረጋግጠናል፡፡
በክልሉ ኢንተርኔት ለምን እንደተቋረጠ ኢትዮ ቴሌኮምም ሆነ የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት እስካሁን ያሉት ነገር የለም፡፡
ኢትዮጵያ ከሰሞኑ በቴሌግራም ላይ እገዳ የጣለች ሲሆን መተግበሪያው በቪፒኤን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ጦርነት መባባሱን ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ላሊበላ እና ጎንደር የሚያደርጋቸውን በረራዎች መሰረዙ ይታወሳል፡፡
የስፔን፣ ፖላንድ እና በርካታ ሀገራት ኢምባሲዎች ዜጎቻቸው ወደ አማራ ክልል እንዳይጓዙ በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው፡፡
ከወራት በፊት በኦሮሚያ ክልል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አጋጥሟት የነበረዉን የመከፋፈል ድርጊትና የጳጳሳት ሹመነትን በሚመለከት በተለያዩ አካባቢዎች የተነሳዉን ተቋዉሞ ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ እግዱ ተጥሎ ለአምስት ወራት መቆየቱ ይታወሳል።
በዚህም መሰረት እንደ ፌስቡክ ፣ ቲክቶክ ፣ ቴሌግራም ፣ ኢንስታግራም ፣ ዩቲዩብ እና ሌሎች የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ሰዎች VPN ( virtual private network ) ቪፒኤንን በመጠቀም ሲገለገሉ ቆይተዋል።
ኢትዮጵያ ለአምስት ወራት በተወሰኑ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ እገዳ በመጣሏ ስምንት ቢሊዮን ብር ገቢ ማጣቷን ኔት ብሎክስ የተሰኘው የቴክኖሎጂ ተቋም አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ በርካታ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ተቋማት መንግሥት በኢንተርኔት ላይ የጣለውን ገደብ እንዲያነሳ ሲያሳስቡ ቆይተዋል።