የቤቶቹ ግንባታ በ68 የሪል ኢስቴት አልሚዎች እንደሚገነባ የተገለጸ ሲሆን መንግሥት መሬት በነጻ ለማቅረብ ተስማምቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመንግሥትና በግል አጋርነት ፕሮጀክት አማካይነት በመረጣቸው ሪል ስቴት አልሚዎች፣ ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ ወጪ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ሊካሄድ ነው ተብሏል።
በዚህ ፕሮግራም ሥር እንዲሳተፉ 68 ሪል ስቴት አልሚዎችን የመረጠ ሲሆን፤ አልሚዎቹም በተቀመጠው 70/30 አጋርነት መሠረት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ተጣምረው ግንባታውን ለማካሄድ ውል መግባታቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።
ከእነዚህም አልሚዎች ውስጥ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ፣ ኦቪድ ግሩፕ፣ ፍሊንትስቶን ሆምስ፣ እንይ ኮንስትራክሽን፣ ጊፍት ሪል ስቴትና ሌሎችም ይገኙበታል።
የከተማ አስተዳደሩ የቤቶቹን ግንባታ ለማካሄድ የሚያስፈልገውን መሬት ከሊዝ ነፃ ማቅረብና መሠረተ ልማቶችን የማሟላት ኃላፊነት አለበት ተብሏል።
የሪል ስቴድ ድርጅቶች ወይም አልሚዎቹ ያስገቡትን የመገንባት አቅም መሠረት ተደርጎ በሚቀርብላቸው መሬት ላይ ወጪውን በመሸፈን ቤቶቹን እንደሚገነቡ ተገልጿል።
አልሚዎቹ የቤቶችን ግንባታ አካሂደው ካጠናቀቁ በኋላ፣ 30 በመቶውን ለከተማ አስተዳደሩ ለማስረከብ መስማማታቸው ታውቋል።
በዚህም መሠረት የከተማ አስተዳደሩ በ2016 በጀት ዓመት 100 ሺሕ ቤቶችን ለማስገባት ማቀዱ ተጠቁሟል።
ከዚህ ውስጥ አቪድ ግሩፕ ተቋራጭ 60 ሺሕ ቤቶችን፤ ጊፍት ሪል ስቴት 12 ሺሕ ቤቶችን፤ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ 10 ሺሕ ቤቶችን ለመግንባት ውል መግባታቸውን ከተማ አስተዳደሩ ገልጿል።
ለቤቶቹ ግንባታ የተለዩ ሦስት አካባቢዎች የተመደቡ ሲሆን፤ እነሱም በከተማ ውስጥ፣ በከተማ አቅራቢያና ከከተማ ወጣ ያሉ ናቸው።
የከተማ አስተዳደሩ በመንግሥትና በግል አጋርነት ለሚካሄደው የቤት ግንባታ ፕሮጀክት፣ በመሀል አዲስ አበባ 350 ሔክታር መሬት ማዘጋጀቱም ተገልጿል።
የፕሮጀክቱ ፋይናንስ ሙሉ በሙሉ የሚሸፈነው በአልሚው ድርጅት ሲሆን፤ የግብዓት አቅርቦት፣ የመብራትና የውኃ፣ እንዲሁም ለግንባታ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች እጥረት ሲፈጠር አልሚ ድርጅቶቹ ቅድሚያ እንዲያገኙ የማድረግ ኃላፊነት የከተማ አስተዳደሩ መሆኑም ታውቋል።