የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ፤ ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ የካንሰር ሕክምና ለማግኘት ወረፋ የሚጠብቁ መኖራቸውን አስታውቋል።
የሆስፒታሉ የካንሰር ሕክምና ማዕከል ክፍል ኃላፊ ዶክተር ኤዶም ሰይፉ እንዳሉት “የተለያዩ የካንሰር ሕክምና ለማግኘት የሚጠብቁ ከ2013 መጨረሻ፣ 2014 ዓ.ም. እና 2015 ዓ.ም. ወረፋ ያልደረሳቸው አሉ፡፡
ይሁን እንጂ በየዕለቱ የሚመጡ ድንገተኛ የካንሰር ታካሚዎች በመኖራቸው በቅድሚያ ለእነዚህ ታካሚዎች አገልግሎቱን እንዲያገኙ ይደረጋል።
በሆስፒታሉ ቆይተው መታከም ይችላሉ ተብለው የተለዩት ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ ሕክምና ለማግኘት እየተጠባበቁ ያሉትን ለማስተናገድ ጥረት እየተደረገ ነውም ብለዋል።
ለዚህ ወረፋ መብዛት ዋነኛ ምክንያት ብለው ያቀረቡት በሆስፒታሉ የሚገኘው መሣሪያ አንድ ብቻ በመሆኑ እንደሆነም ዶክተር ኤዶም ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት ብቻ በተደረገው ማጣራት የካንሰር ሕክምና ለማግኘት የሚጠበባቁ 5,000 ታካሚዎች ሲኖሩ፣ በማዕከሉ በቀን በአማካይ ከ300 በላይ ታካሚዎች ይስተናገዳሉም ብለዋል።
ከእነዚህ የካንሰር ታካሚዎች መካከል 70 በመቶ የጨረር ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ሲሆኑ፣ ኬሞ ቴራፒ የሚያስፈልጋቸው የታካሚዎች ቁጥር ቀላልም የሚባል አይደለም ።
በማዕከሉ አገልግሎት ለማግኘት የ2014 ዓ.ም. እና በ2015 ዓ.ም. ሕክምና ለማግኘት የተመዘገቡ ደግሞ ከ10,000 በላይ ናቸው። “
በኢትዮጵያ የካንሰር ህክምና ከአዲስ አበባ ውጪ በጎንደር እና በሀረማያ ሆስፒታሎችም በመሰጠት ላይ ቢሆንም የህክምና ፈልጊዎች እና የህክምና ቁሳቁሱ አይመጣጠንም ተብሏል።