ኢትዮጵያ የህዳሴው ግድብ ውሀ መያዣ ጊዜን አራዘመች

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እስከ መስከረም ውሀ እንደማይዝ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ተናግረዋል።

ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ እየሰጡ ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ ከአባላቱ ለተነሳላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በዚህ ጊዜ እንዳሉት የኢትዮጵያ ህዳሴው ግድብ ውሀ ሙሌት አይከናወንም ብለዋል።

“ኢትዮጵያ የሱዳንን እና ግብፅ ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ የህዳሴ ግድብ ሙሌቱ እስከ መስከረም መጀመሪያ አታከናውንም” ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከሀምሌ ወር ጀምር ውሀ ሲይዝ የቆየ ሲሆን ዘንድሮ ግን ውሀ የመያዣው ጊዜ ወደ መስከረም መዛወሩ ተገልጿል።

እንደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ገለጻ የዘንድሮው ውሀ ሙሌት ወደ ግብጽ እና ሱዳን በቂ የዉሃ ከደረሰ በኋላ ሙሌቱ ይከናወናል።

12 ዓመታትን ያስቆጠረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሁለት ተርባይኖቹ ሀይል በማመንጨት ላይ ናቸው።

ሱዳን እና ግብፅ በተደጋጋሚ በህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ አሳሪ ስምምነት እንዲፈጸም ፍላጎት እንዳላቸዉ ሲገልጹ ቆይተዋል።

በተያያዘ ዜና የተለያዩ የውጭ ሀገራት ሁለት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያንን ለመቅጠር ፍላጎት ማሳየታቸውን ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል ።

በሀገራቱ ፍላጎት መሰረትም የስራ ውል ስምምነት እየተፈረመ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚንስትሩ ተጨማሪ ዜጎችን ወደ ውጭ ሀገራት ለመላክ ጥረቶች እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በዘንድሮው ዓመት ብቻ በስራ እና ክህሎት ሚንስቴር አማካኝነት ከሳውዲ አረቢያ፣ ኩዌት፣ ጆርዳን እና ሌሎችም ሀገራት ጋር የስራ ስምምነት ፈጽማለች ተብሏል።

ባለፉት 11 ወራት ውስጥ 3 ነጥብ 1 ሚሊየን ገደማ ሰዎች ስራ መያዛቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚንስትሩ በግብርና ዘርፍ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ፣ በኢንደስትሪ ዘርፍ 600 ሺህ የገልግሎት ዘርፍ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎች ስራ መያዛቸው ተገልጿል።

እንዲሁም ወደ ውጭ ሀገራት ደግሞ 100 ሺህ ኢትዮጵያዊያን ተልከዋልም ተብሏል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *