አፍሪካ ከዶላር ይልቅ በራሷ ገንዘብ እንድትገበያይ የኬንያ ፕሬዝዳንት ጠየቁ

ኬንያ የአፍሪካ ሀገራት የእርስ በርስ ግብይት ሲፈጽሙ እና አገልግሎት ሲለዋወጡ በራሳቸው ገንዘብ ክፍያ  መፈጸም እንዲጀምሩ ጠይቃለች።

ለኢጋድ የመሪዎች ስብሰባ ጅቡቲ ያመሩት የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ አፍሪካ በዶላር ላይ ያላት ጥገኝነት ይብቃ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

“ከጂቡቲ እቃ ገዝተን በዶላር የምንከፍለው ለምንድን ነው? ለምን? ምንም ምክንያት የለም”  ያሉት ፕሬዝዳንት ሩቶ ጂቡቲም ሆነች ኬንያ የእርስ በርስ ግብይት ሲፈጽሙ የአሜሪካ ዶላር መጠቀም አያስፈልጋቸውም ብለዋል።

“እኛ የአሜሪካን ዶላር እየተቃወምን አይደለም፤ በነጻነት ግብይት መፈጸም ስለፈለግን እንጂ” ሲሉም ስለ ዶላር አስፈላጊነት ተናግረዋል።

እንደ ኢስት አፍሪካን ጋዜጣ ዘገባ ፕሬዝዳንቱ ሩቶ አክለውም “ዶላር የሚያስፈልገን ከአሜሪካ ጋር ለምናደርገው ግብይት ብቻ ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በፈረንጆቹ 1993 የተቋቋመው የአፍሪ ኤክዚም ባንክ ግብይቱ በየሀገራቱ ገንዘብ እንዲከናወን የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱንም ፕሬዝዳንቱ አንስተዋል።

ኬንያ በዚሁ ባንክ የተዋወቀውን የፓን አፍሪካ የክፍያ ስርአት ቀድማ ወደ ስራ እንደምታስገባም ፕሬዝዳንት ሩቶ አረጋግጠዋል፡፡

የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ከዶላር ውጭ በገንዘባቸው ግብይት የሚፈጽሙበትን ዝርዝር ጉዳይ በጂቡቲ በተካሄደው 14ኛው የኢጋድ የመሪዎች ጉባኤ ሳይመከርበት እንዳልቀረ ዘገባው ያመላክታል።

ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ችግር ያለባቸው የአፍሪካ ሀገራት የእርስ በርስ የንግድ ትስስራቸውን ለማጠናከር የኬንያ ጅምር መልካም ውጤት እንደሚያመጣ ይጠበቃል።

ሩሲያ በቀጣይ በሱቺ ከሚካሄደው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ በኋላ ከአፍሪካ ጋር የሚኖራትን ግብይት ከዶላር ውጪ ማድረግ እንደምትጀምር ተናግራለች፡፡

በዓለማችን ከ6 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ንግድ በአሜሪካ ዶላር ቢካሄድም ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ዝቅተኛው ሆኖ መመዝገቡን የአለም አቀፉ የፋይናንስ ተቋም (አይኤምኤፍ) መረጃ ያሳያል፡፡

ሩሲያ፣ ቻይና ሳውዲ አረቢያ እና ህንድን ጨምሮ የምዕራባውያን ጫና ያረፈባቸው ሀገራት ዶላርን በመተው በራሳቸው ገንዘብ መገበያየት ጀምረዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *