የአክሱም ሀውልት ዳግም ለጎብኚዎች ክፍት መደረጉን በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የአክሱም ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
የጽሕፈት ቤቱ ሀላፊ ገብረመድህን ፍፁም ብርሀን፤ በአክሱም ከተማና አካባቢው የሚገኙ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ጥንታዊ ቅርሶች ለቱሪስቶች ክፍት መደረጋቸውን ተናግረዋል።
ቅርሶቹ ዳግም ለጎብኚዎች ክፍት እንዲሆኑ ሕብረተሰቡ በጉልበቱ፣ በገንዘቡና በሙያው ያደረገው ተሳትፎ የላቀ እንደነበርም ገልጸዋል።
የቱሪዝሙን ዘርፍ ወደነበረበት ለመመለስና ሕብረተሰቡ ለቱሪስቶች የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሳደግ ለፎቶ ግራፍ ባለሙያዎች፣ አስተርጓሚዎች፣ ለባህላዊ ጌጣጌጦችና ቅርፃ ቅርፅ ባለሙያዎች እንዲሁም ለባለ ሆቴሎች ስልጠና መሰጠቱንም አስረድተዋል።
በአክሱምና አካባቢው የሚገኙ ቅርሶችና ሙዚየም ለጎብኚዎች ተደራሽ ለማድረግ ከዛሬ ጀምሮ ክፍት መደረጋቸውን ገልጸዋል።
በአክሱምና አካባቢው የሚገኙ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ጥንታዊ ቅርሶች ለመጎብኘትና ለማየት በየዓመቱ ከ30 ሺሕ በላይ የውጭ አገር ቱሪስቶች ይጎበኙት እንደነበር አስታውሰዋል።
ጎብኝዎቹ በአክሱምና አካባቢ በሚኖራቸው ከ2 እስከ 3 ቀናት ቆይታ ከሚያገኙት አገልግሎት የቱሪዝም ጽህፈት ቤቱና ነዋሪው በዓመት ከ180 ሚልዮን ብር በላይ ገቢ ያገኝ እንደነበረም ጠቅሰዋል።
በባህላዊ ቅርጻ ቅርፅ ዘርፍ ተሰማርቶ ኑሮውን ሲደጉም የነበረው ወጣት እዝግነአምን ኪዳነ፣ በተፈጠረው ሰላም የቱሪዝሙ ዘርፍ እንቅስቃሴ መጀመሩ የሚሰራውን የቅርፃ ቅርጽ ሥራ አጠናክሮ በመቀጠል የራሱንና የቤተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል እንደሚተጋ አብራርቷል።
በሰፌድና አለላ ሥራ ተሰማርታ ከጎብኚዎች ገቢ ታገኝ የነበረችው ወጣት አዜብ አሰፋ፤ በዓመት እስከ 100 ሺሕ ብር ገቢ ታገኝ እንደነበረ አስታውሳ አሁን በተፈጠረው ሰላም የቀድሞ ሥራዋን አጠናክራ ለመቀጠል መዘጋጀቷን ገልጻለች ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
በዓለም ቅርስነት በተመዘገበው አክሱምና አካባቢው በርካታ የተለያየ ቅርጽና ዲዛይን ያላቸው ከአንድ ወጥ ድንጋይ የተሰሩ ሀውልቶች መኖራቸው ይታወቃል።