(ኢትዮ ነጋሪ፣ መጋቢት 28 ቀን 2015 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ) “ዛሬን በንቃት፣ ነገን በስኬት” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው ይህ ሃገር-አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ከሚያዚያ 21 እሰከ 22 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል ተበሏል፡፡
ፌስቲቫሉ በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅተ የገንዘብ ድጋፍ በሚተገበረው ከፍታ የተቀናጀ የወጣቶች ፕሮግራም በኩል የሚዘጋጅ ሲሆን አምሬፍ ሄልዝ አፍሪካ ከአጋሮቹ እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ፌስቲቫሉን እንደሚመራ ተገልጿል፡፡
የከፍታ የተቀናጀ የወጣቶች ፕሮግራም ቺፍ ኦፍ ፓርቲ አቶ ቻላቸው ጥሩነህ እንዳሉት ወጣቶችን በተለያዩ መስኮች ብቁ ማድረግ የዚህ ፌስቲቫል ዋና አላማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ፌስቲቫሉ የወጣቶች ስኬት ዕውቅና የሚሰጥበት፣ ከተለያዩ ዘርፎች የመጡ ወጣቶች ልምድ የሚለዋወጡበት፣ እንዲሁም ለበለጠ ስኬት ተነሳሽ የሚሆኑበት መሆኑንም አቶ ቻላቸው አክለዋል፡፡
በዚህ ፌስቲቫል ላይም ከ10 ሺህ በላይ ወጣቶች ይሳተፋሉ የተባለ ሲሆን የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የሚጎበኙበት፣ የወጣት ተዕጽኖ ፈጣሪዎችን ተሞክሮ የሚጋሩበት፣ ጠቃሚ ውይይቶችን የሚያደርጉበት፣ በመዝናኛ ፕሮግራሞች የሚሳተፉበት፣ እንዲሁም ንግድን ጨምሮ የተለያዩ ትርዒቶች ላይ በመካፈል እውቀትን፣ ክህሎትን እና ልምድን የሚያገኙበት ይሆናልም ተብሏል፡፡
ፌስቲቫሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶችን በልዩ ልዩ መንገድ ለመደገፍ በመጋቢት 2014 ዓ.ም በይፋ የተጀመረው የዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ የተቀናጀ የወጣቶች ፕሮግራም ትግበራ አካል ነው የተባለ ሲሆን ፕሮግራሙ በ18 የኢትዮጵያ ከተሞች በመተግበር ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም ይህ ፕሮግራም ወጣቶች ትርጉም ባለው መልኩ ከኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ዕድሎችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ፤ ለወጣቶች አስፈላጊ እና ምቹ የሚባሉ አገልግሎቶች በስፋት ተደራሽ እንዲሆኑ በመስራት ላይ ነው ተብሏል።
ፌስቲቫሉ ከ15 እስከ 29 የዕድሜ ክልል ላይ ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች የተዘጋጀ ሲሆን በወጣት-ነክ ርዕሰ-ጉዳዮች ዙሪያ ተሰሚነትን ለመጨመር፤ በወጣቶች መካከል የሚደረጉ የልምድ ልውውጥ እና የመማማር ዕድሎችን ለማበረታታት ታስቦ እንደተዘጋጀ አቶ ቻላቸው አክለዋል፡፡