መንግሥት የአማራ ልዩ ሀይልን ጨምሮ የሁሉንም ክልል ልዩ ሀይሎች ትጥቅ እያስፈታ መሆኑን ገለጸ

መንግሥት የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ የሚያስችል አንድ ጠንካራ የተማከለ ሠራዊት ለመገንባት አቅጣጫ ማስቀመጡን ዛሬ ምሽት ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

በዚህ መሠረት የየክልሉን ልዩ ኃይሎች ወደ ተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ የሚያስችላቸውን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማካሄድ መጀመሩን አሳውቋል።

በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የልዩ ኃይል አባላት እንደ ምርጫቸውና እንደ ፍላጎታቸው ፣በመከላከያ፣ በፌደራል ፖሊስ
፣በክልል ፖሊስ አባልነት መካተት ይችላሉ ብሏል።

በዚህ ሐሳብ ላይም ከልዩ ኃይል አመራሮችና አባላት ጋር ከመግባባት ላይ መደረሱን ገልጿል።

ቀደም ብሎም በሁሉም ክልል አመራሮች ጥናት ተደርጎበት፣ በተገኘው ውጤት ያለምንም ልዩነት ውሳኔው ስምምነት ተደርሶበታል ሲል አስታውሷል።

የክልል ልዩ ኃይልን በተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች የማካተት ውሳኔና የተግባር እንቅስቃሴ በጥናት ላይ ተመሥርቶ የሚከናወን ነው ያለው መንግስት ” ይህ አካሄድ የኢኮኖሚ ዐቅማችን በማሰባሰብ የሠራዊታችንን የሥልጠና፣ የትጥቅ እና የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ከፍተኛ ፋይዳ አለው፤ ይሄንን በመረዳትም በሁሉም ክልሎች ሂደቱ በመግባባትና በውይይት እየተከናወነ ይገኛል ” ብሏል።

ነገር ግን በ ” አማራ ክልል ”  በሚገኙ የተወሰኑ የልዩ ኃይል ክፍሎች ውስጥ ሂደቱን የሚያውኩ ተግባራት መታየታቸውን ገልጿል።

ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ የመልሶ ማደራጀት ሥራውንና ዓላማውን በአግባቡ ባለመረዳት፤ በሌላ በኩል የጥፋት አጀንዳ አራጋቢዎች ሆን ብለው በሚነዙት የሐሰት ወሬ በመጠለፍ ነው ሲል አስረድቷል።

መንግስት በመግለጫው ፤ ” ከሚነዙት የሐሰት አጀንዳዎች መካከል፤  የመልሶ ማደራጀቱ መርሐ ግብር በአማራ ክልል ብቻ እየተካሄደ ነው፤  ሕወሐት ትጥቅ ሳይፈታ እንዴት የክልሉ ልዩ ኃይል ትጥቅ ይፈታል የሚሉትና ሌሎችም ይገኙበታል ” ብሏል።

” የክልል ልዩ ኃይል አባላትን ወደ ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች የማስገባት ፕሮግራም በመላ ሀገሪቱ የሚተገበር ነው። ” ያለው መንግስት ” ሥራውም በሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ ጊዜ እየተካሄደ የሚገኝ ነው። ሂደቱንም መንግሥት በጥናት፣ በዕቅድ እና በጥንቃቄ እየመራው ይገኛል። ” ሲል አሳውቋል።

ወደ ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች የማስገባት ተግባር በሚፈጸምበት ጊዜ በክልሎች አስተማማኝ ሰላምና ጸጥታን ለማረጋገጥ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በሁሉም ቦታዎች ሥምሪት መውሰዱ ተገልጿል።

በሌላ በኩል ሕወሐት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንዲፈታ እየተደረገ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ብሏል።

” የሕወሐት ትጥቅ የመፍታት ሂደት በተፈረመው ስምምነት መሠረት ያለማወላወል የሚፈጸም እንጂ ከሌላ ሀገራዊ ዕቅድ ጋር የሚቀናጅም የሚጣረስም አይደለም።

የሂደቱ ዋና ዓላማ የትኛውንም ልዩ ኃይል ትጥቅ ማስፈታት አይደለም ” ሲል መንግስት አስረድቷታ።

ዋናው አላማ ልዩ ኃይሉ ትጥቁን ይዞ እና የተሻለ ዐቅም ተፈጥሮለት በምርጫው መሠረት የክልል ፖሊስን፣ የፌደራል ፖሊስን ወይም የሀገር መከላከያ ሠራዊትን እንዲቀላቀል ማድረግ ነው።

በዚህ ሂደት መካተት የማይፈልግ ማንኛውም የልዩ ኃይል አባል ካለ መብቱ ተጠብቆ ወደ መደበኛ የሲቪል ሕይወት እንዲገባ መንግሥት አስፈላጊውን የማቋቋም ሥራዎች ይሠራል ፤ እንዲቋቋምም ድጋፍ ያደርጋል ብሏል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *