ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ የቀረበባትን ክስ ውድቅ አደረገች

ሶማሊላንድ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ልዩ ኃይሎች ድንበር አልፈው በሶሎ ግዛት ላስአኖድ ከተማ ጦርነት ውስጥ እየተሳተፉ ነው ስትል ክስ አቅርባ ነበር።

በፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ የሚመራው የሶማሌላንድ ካቢኔ ባወጣው መግለጫ ግጭት ባለባት ላስአኖድ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ኃይሎች በተጨማሪ የሶማሊያ እና የፑንትላንድ ወታደሮች ይገኛሉ ብሏል፡፡

ካቢኔው የሶማሌ ላንድን ዓለም አቀፋዊ ድንበር አልፈው ገብተዋል ያላቸው እነዚህ ኃይሎች ከአካባቢው እንዲወጡም አሳስቧል። 

ለሶማሊላንድ ክስ ምላሽ የሰጠው የሶማሌ ክልል መንግስት በላሳኖድ ከተማ በሚካሄደው ጦርነት አንድም የሶማሌ ክልል ኃይል አባል የለም ያለ ሲሆን፣ መግለጫውንም ኃላፊነት የጎደለው ውንጀላ እንደሆነ ገልጿል፡፡

በጉዳዩ ላይ የተናገሩት የሶማሌ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ዐብዱልቃድር ረሺድ ‹‹እኛ የሌላ ሀገር ፖለቲካ ውስጥ እጅ የምናስገባበት ምንም አይነት ተልዕኮ የለንም፤ እሳቤውም የለንም። ስለዚህ ያወጡት መግለጫ እኛን የማይመለከተን ነው›› ሲል አስታውቋል።

በአወዛጋቢዋ ላስአኖድ ጥር መጨረሻ ላይ የተቀሰቀሰው ይህ ግጭት ከቀሪው የሶማሊያ ክፍል በተለየ በተረጋጋ ሁኔታ በሰላም ውስጥ የቆየችውን የሶማሊላንድን ሰላም አናግቷል።

ግዛቲቱ ዋነኛ የንግድ መስመር ስትሆን ሶማሊላንድ እና ቀሪው አጎራባች በሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት ስር ያለችው ከፊል ራስ ገዝ አስተዳደሯ ፑንትላንድ በይገባኛል ሲወዛገቡባት ቆይተዋል።

በቅርቡም ላስ አኖድ በምትገኝበት የሱል ክልል የጎሳ መሪዎች የሶማሊያን የፌደራል መንግሥት እንደሚደግፉ እና የሶማሊላንድ ባለሥልጣናት ወታደሮቻቸውን ከአካካቢው እንዲያስወጡ መግለጫ አውጥተዋል።

ከሱል ክልል በተጨማሪ በሌሎች ሁለት ግዛቶች የሚገኙ የአገር ሽማግሌዎች ወደ ሶማሊያ መቀላቀል እንደሚፈልጉ መግለጻቸውን ተከትሎ ነበር አዲሱ ግጭት የተቀሰቀሰው፡፡

በሶማሊላንድ እና ለሶማሊያ ታማኝ በሆኑ የአካባቢው የጎሳ ኃይሎች መካከል ነግሶ የነበረው ውጥረትም ወደ ግጭት ተቀይሮ ቢያንስ የሁለት መቶ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *