03
May
በሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መኖሪያ በሆነው የክሪምሊን ቤተ መንግስት ላይ የድሮን ጥቃት መፈጸሙን አርቲ ዘግቧል፡፡ የድሮን ጥቃቱ ያነጣጠረው በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ ሲሆን ጥቃቱ ሲፈጸም ፕሬዝዳንቱ በቦታው አልነበሩም ተብሏል፡፡ የቤተ መንግስቱ ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔስኮቭ እንዳሉት አደጋው በሁለት ድሮኖች የታገዘ ሲሆን የየት ሀገር ስሪት እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም፡፡ በድሮኖቹ ጥቃት የተጎዳ ሰው አለመኖሩን የተናገሩት ቃል አቀባዩ ሞስኮ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ መጀመሯንም አክለዋል፡፡ የሞስኮ ከተማ ከንቲባ በበኩላቸው በከተማዋ ከተፈቀደላቸው የደህንነት ተቋማት ውጪ የድሮን እንቅስቃሴ መታገዱን ገልጸዋል፡፡ ፊንላድን እየጎበኙ ያሉት የዩክሬን ፕሬዝዳንት ከሄልስንኪ እንዳሉት በክሪምሊን ቤተ መንግስት ላይ ተፈጸመ ስለተባለው የድሮን ጥቃት መረጃ የለኝም ብለዋል፡፡