የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ባለበት እንዲቀጥል ከስምምነት ላይ ተደረሰ

ከአንድ ወር በላይ የቆየው የሀገራዊ ምክክር ተመካካሪዎች እየተወያዩባቸው ካሉ ጉዳዮች መካከል የሰንደቅ አላማ ጉዳይ አንዱ ሲሆን አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለም ባለበት እንዲቀጥል ነገር ግን መሀሉ ላይ ያለው አርማ እንዲቀየር ከስምምነት ላይ ተደርሷል።

ከ8ቱም ቡድኖች በተመረጡ አጠናቃሪዎች የተዋቀረው አዘጋጅ ቡድን እያንዳንዳቸው 500 ሰዎችን ከያዙ 8 ቡድኖች ተቀብሎ ያጣጣማቸውን፣ ድግግሞሽ እንዳይኖር ያስወገደላቸውን የአጀንዳ ምክረ ሀሳቦች አዘጋጅቶ የ8ቱንም ቡድኖች ምክረ ሀሳቦች የያዘ ቃለጉባዔ ለ8ቱም ቡድኖች አቅርቧል።

ተመካካካሪዎች በተለያዩ ቡድኖች ተደራጅተው ሀሳብ ከማመንጨት እስከ በሀሳቦቹ መከራከር ድረስ ከመከሩባቸው ስምንት አጀንዳዎች መካከል የሀገር ግንባታ አጀንዳ አንዱ ሲሆን፣ በዚሁ አጀንዳ በዛሬው ቃለጉባዔ ከተነሱት ምክሮች መካከል የቋንቋ ጉዳዮችተጠቃሽ ናቸው።

የቋንቋ ጉዳይን በተመለከተ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቋንቋ ይኑራት? ወይስ አይኑራት? እና ይኑራት ከተባለ ደግሞ አማርኛ ይሁን፣ አፋን ኦሮሞ ይሁን የሚሉ ምክረ ሀሳቦች ከተመካካሪዎች ቀርበው ሲያከራክሩ ሰንብተዋል።

ከ8ቱም ቡድኖች የተመረጡ 120 አባላት ያሉት በምክረ ሀሳቦቹ አንድ ወጥ አጀንዳ የሚያዘጅ ቡድን እያንዳቸው 500 ሰዎች ለያዙት ቡድኖች 8ቱም ቡድኖች ባነበበው ቃለጉባዔ መሰረት ደግሞ፣ “አሁን ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ ብሔራዊ ቋንቋ አያስፈልገንም” የሚለው ስምምነት ተደርሶበታል ተብሏል።

“ሲያስፈልግ እንደ ሁኔታው ታይቶ ካሉት ቋንቋዎች አስፈላጊው ሊደረግ ይችላል” የሚል ምክረ ሀሳብም ተያይዞ ቀርቧል።

የፌዴራል የሥራ ቋንቋን በተመለከተ ደግሞ፣ መጀመሪያ አምስት ቋንቋዎች ቀርበው፣ በኋላ ደግሞ ወደ 13 ቋንቋዎች የኢትዮጵያ የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ ተመካካሪዎች ምክረ ሀሳብ ሲያቀርቡ ነበር።

በተነበበው ቃለጉባዔ ደግሞ፣ አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ፣ አፋርኛ፣ሶማሊኛ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ፣ በቀጣይነት ሌሎችም እንዲከቱ የሚል ሀሳብ በአመዛኙ ተመካካሪዎች መቅረቡን ተሳታፊው ተናግረዋል።

የሰንደቅ አላማን ጉዳይ በተመለከተ ተመካካሪዎች አሁን ያለው ይቀጥል፤ አርማው ይቀየር፣ ሲቀየር ደግሞ የሕዳሴ ግድብ ይሁን፣ የዓድዋ ድል፣ የእርግብና ሌሎች ይሁን የሚሉ አማራጭ ምክረ ሀሳቦች ከጉባያተኞች ቀርበው ነበር።

“አሁን ያለው ይቀጥል እና አርማው አካታች በሆነ መልኩ ለወደፊት ይታይ” የሚሉ ሁለት ምክረ ሀሳቦች መቅረባቸው ተገልጿል።

“አካታች በሆነ መልኩ” ሲባል “ህዝቡ ለወደፊት ቀርቦ እንዲወስን” መባሉ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙርን በተመለከተ አሁን ያለው “ብሔራዊ መዝሙር እንዳለ ይቀጥል” የሚለው ምክረ ሀሳብ ከስምምነት ተደርሶበታል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *