ባሕርዳር ስታዲየም ዓለም አቀፍ ውድድሮችን እንዲያካሂድ ተፈቅዶለታል።
የባሕርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዬም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መስፈርቶችን በማሟላት ዓለም አቀፍ ውድድሮችን እንዲያካሂድ ፈቃድ አግኝቷል።
ኢትዮጵያ የካፍ እና ፊፋ እውቅና ያለው ስታዲየም ባለቤት ባለመሆኗ ዋልያዎቹን ጨምሮ ክለቦች በውሰት ሜዳዎች ሲጫወቱ ቆይተዋል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የባሕርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዬም መስፈርቶችን ባለማሟላቱ ዓለምአቀፍ ጨዋታዎችን እንዳያደርግ አግዶት ቆይቷል።
በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሌሎች ሀገራት እንዲጫወት ተገድዶ ቆይቷል።
ካፍ የባሕርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዬም የዓለም አቀፍ ስታዲዬም ማሟላት የሚገባውን መስፈርት እንዲያሟላ አቅጣጫ ማስቀመጡ ይታወሳል።
ባለፉት ዓመታት ስታዲዬሙ የካፍ መስፈርቶችን ባሟላ መልኩ ግንባታ ሲካሄድለት ቆይቶ አሁን ላይ መስፈርቶችን በማሟላቱ ማረጋገጫ ተሰጥቶታል ተብሏል።
ኢትዮጵያ የካፍ መስራች ሀገር ብትሆንም የስፖርት መሰረተ ልማቶችን ሳታሟላ ቆይታ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ሳታዘጋጅ ቆይታለች።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለስፖርት መሰረተ ልማቶች ከፍተኛ በጀት በመመደብ ከስታንዳርድ በታች የሆኑ ስታዲየሞቿን ደረጃ እያሻሻለች ትገኛለች።
የ2029 ካፍ እግር ኳስ ውድድርን ለማዘጋጀት ፍላጎቷን የገለጸች ሲሆን ከሎሎች ሀገራት ጋርም እየተፎካከረች ትገኛለች።
በአዲስ አበባም 62 ሺህ ተመልካቾችን መያዝ የሚችል አዲስ ስታዲየም ግንባታ በማካሄድ ላይ ስትሆን ግንባታው በአንድ ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።