በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላንና ፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በካርበን ገበያ ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይቷል።
ረቂቅ አዋጁ የተበታተነውን የካርበን ግብይት በአንድ የሕግ ማዕቀፍ ለማስተዳደር እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እየተከናወኑ ያሉ ጅምር ስራዎችን ለማጠናከር እንደሚረዳ በውይይቱ ላይ ተጠቅሷል።
ኢትዮጵያ ለአየር ንብርት ለውጥ ተጋላጭ መሆኗን ያስታወሰው የካርበን ረቂቅ አዋጅ ለአማቂ ጋዝ ልቀት ቅነሳ ደጋፍ ማድረግ እና በአየር ንብርት ለውጥ ላይ አደገኛ ጣልቃ ገብነትን ማስቀረት “የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ነው” ብሏል።
በአስር ክፍል እና በ44 ገጽ የተዘጋጀው ይህ የካርበን ግብይት ረቂቅ አዋጅ የኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ በአለም አቀፍ ደረጃ የተፈራረመችውን ስምምነት ለመተግበርም እንደሚረዳ በአላማዎቹ ስር ተጠቅሷል።
ረቂቁ ስለ ፋይናንስ ድንጋጌዎች በሚዘረዝርበት ክፍል ዘጠኝ ላይ የባንኮችና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ተሳትፎ እና ሚና ሲያስረዳ ፤ ባንኮች እንደየፍላጎታቸው በገዥነት፣ በሻጭነት፣ በግብይት አከናዋኝነት ወይም በአሰባሳቢነት እንዲሳተፉ ይፈቅዳል።
የካርበን አሰባሳቢ የሚለው ሲተረጎም ደግሞ ፤ ከተለያዩ የመሬት ባለይዞታዎች ፣ ኩባንያዎች አነስተኛ የሙቀት አማቂ ጋዞችን የመቀነስ፣ የማስወገድ ወይም የማስቀረት ፕሮጀክቶችን በአንድ ላይ በማሰባሰብ ወደ ልዩ ልዩ ፖርቶፎሊዮዎች በማካተት እንደገና የሚሸጥበትን መንገድ የሚመራ ነው ሲል ተርጉሞታል።
በተጨማሪም ባንኮች የካርቦን ሃብት ፖርቶፊሊዮችን ከአካባቢ እና ከማህበራዊ ስጋት አስተዳደር ማዕቀፎቻቸው ጋር እንዲገናኙ ይበረታታሉ ፣ ከካርበን ክሬዲት ጋር የሚያያዙ ቦንዶችን እና “አረንጓዴ ዋስትናዎችን “ጨምሮ ልዪ የፋይናንስ አግልግሎቶችን ማቀረብ እንደሚችሉም አስረድቷል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ባንኮች ፣ የፋይናንስ ተቋማት በሀገሪቱ ለሚከናወኑ የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት ለመቀነስ ፣ ለማስቀረት አልያም ለማስወገድ ለተቀረጹ ፖሊሲዎች የብድር ፋይናንስ ፣ የኢኪዮቲ ኢንቨስትመንት እና የብድር ገጽታ፣ ማሻሻያዎችን ሊያቀርቡ እንደሚችሉም በረቂቁ ተደንግጓል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት ለካርበን ክሬዲቶች ግብይት ፣ ዝውውር እና ክፍያ እንደ ማሳለጫ ወይም ባለዳራዎች መሆን እንደሚችሉም ተጠቅሷል።
በዚህ የካርበን ገበያ ረቂቅ አዋጅ ላይ በቀጣይ ተጨማሪ የሕዝብ ይፋዊ ውይይቶች መካሄዳቸው እንደሚቀጥልም ተገልጿል።
ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የአረንጓዴ ሌጋሲ ፕሮጀክቶችን ቀርጻ በየ ዓመት አራት ቢሊዮን እና ከዛ በላይ ችግኞችን በነትከል ላይ ስትሆን የካርበን ሽያጭ በኦሮሚያ እና ደቡብ ምዕራብ ክልሎች ከ200 ሚሊዮን በላይ ዶላር ለዓለም ባንክ እና ኖርዌይ መሸጧ አይዘነጋም።