ኢትዮጵያዊቷ እመቤት መሀባው ለምርምር ወደሕዋ እንድትጓዝ ተመረጠች

በአሜሪካ ሀገር የሚገነውና በሕዋ ሳይንስ ምርምር ላይ የሚሰራው ‘ታይታንስ ስፔስ ኢንዱስትሪ’ በ2029 ወደጠፈር ለሚያደርገው ጉዞ ኢትዮጵያዊቷን እመቤት መሀባውን ከተጓዥ ተመራማሪዎች መካከል አንዷ እንድትሆን መርጧታል፡፡

እመቤት መሀባው ከልጅነቷ አንስቶ ለሕዋ ሳይንስ ፍቅር እንደነበራት የተገለጸች ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን እየተከታተለች ሳለ በሕዋ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ስኮላርሺፕ አግኝታ ወደሕንድ አቅንታለች።

በኋላም አሜሪካ ውስጥ በሕዋ ሳይንስ ምርምር ላይ የሚሰራውን ታይታንስ ስፔስ ኢንዱስትሪን መቀላቀሏን ተከትሎ፤ በተቋሙ በኤሮስፔስ ኢንጂነርነት ሙያዋ የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን እያከናወነች ይገኛል።

የምትሰራበት የሕዋ ምርምር ተቋም በእ.አ.አ. በ2029 ወደጠፈር ለሚያደርገው ጉዞ እመቤት መሀባውን ከተጓዥ ተመራማሪዎች መካከል አንዷ እንድትሆን መርጧታል።

ለዚህ ምርጫ የተለያዩ መስፈርቶች ቢኖሩትም፤ ግዳጁን ለመፈፀም በአካል፣ በስነልቦናም ሆነ በምርምር ሥራዋ ብቁ መሆኗ ካስመረጧች ምክንያቶች መካከል ዋነኞቹ መሆናቸውን ገልጻለች ተብሏል።

ወጣቷ የሕዋ ሳይንስ ባለሙያ ለጠፈር ጉዞዋ የሚረዳትን የተለያዩ ዝግጅቶች እያደረገች ሲሆን፤ በቡድን የሚደረገውን ዝግጅት ደግሞ እ.አ.አ. በ2026 አካባቢ እንደምትጀምር ገልጻለች።

በምድር ምህዋር ላይ በመሽከርከር የተለያዩ ምርምሮችን ማከናወንን የሚያካትተውን የሕዋ ጉዞ ዕድሉን የኢትዮጵያን ሥም ከፍ ለማድረግ እንደምትጠቀምበት ተናግራለች።

በተለይም ወደሕዋ በሚኖራት ጉዞ ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ይዛ የመሄድ ፍላጎት እንዳላትም አሳውቃለች።

በተለያዩ ዓለም አቀፍ ደረጃዎች ዕውቅና እያገኘች የመጣችው እመቤት፤ ለስፔስ ጄኔሬሽን አድቫይዞሪ ካውንስል የኢትዮጵያ ተወካይ በመሆን እያገለገለች ይገኛል። ከአፍሪካ ስፔስ ሊደርስ አዋርድ በ2024 ከአፍሪካ 4 ተሸላሚ ወጣቶች መካከል አንዷም ነበረች።

ዓለም አቀፉ አስትሮናውቲካል ፌዴሬሽንም በ2025 ተስፈኛ ከሆኑ የሕዋ ሳይንስ ባለሙያዎች መካከል አንዷ መሆኗንም አሳውቋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *