ኢትዮጵያ ለካንሰር ህመምተኞችን ለማከም የሚውሉ መድኃኒቶችን ሙሉ በሙሉ ከውጪ በማስገባት ላይ ትገኛለች።
ይሁንና እነዚህን መድኃኒቶች በሀገር ውስጥ ለማምረት የአዋጭነት ጥናት በማድረግ ላይ መሆኑ ተገልጿል።
ባለሀብቶች በተለያዩ ዘርፎች የካንሰር መድኃኒቶችን በሀገር ውስጥ እንዲያመርቱ የሚያስችል ፕሮጀክት በቂልንጦ ፋርማሲዩቲካል ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ውስጥ ገብተው በፕሮጀክት ደረጃ ይዘው ስራ መጀመራቸው ተገልጿል።
በቅርብ ጊዜ እነዚህን ፕሮጀክቶች በመደገፍ የፕሮጀክት ጊዜያቸውን አጠናቀው ወደ ምርት እንዲገቡ የአርማሆር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ድጋፍ እንደሚያደርግ በአርማሆር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት የፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር መሳይ ወ/ማርያም ተናግረዋል።
መድኃኒቶች በሀገር ውስጥ መመረት ከመጀመሩ በፊት በሀገር ውስጥ ቢመረቱ ነው ወይስ ከውጪ ቢገቡ የተሻለ የሚሆነው የሚለውን ጥናት ያማከለ እንደሚሆንም ተመራማሪው አክለዋል።
ይሁንና በሀገር ውስጥ መመረት ሲጀምሩ ከውጪ የሚገቡትን ማስቀረት የሚችል በመሆኑ ከፍተኛ አስዋጽኦ እንደሚኖረው ተጠቁሟል።
መንግስት በዘርፉ ከፍተኛ የሆነ ትኩረት እንደሚኖረው እና የመድኃኒት ዋስትና ከማስጠበቅ አንጻር በዘላቂ ሁኔታ ለማምረት የሚያስችል ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተነግሯል።
በሌላ በኩል በመካከለኛው ምስራቅ እየተከሰተ ካለው ግጭት ጋር ተያየዞ በተፈጠረው የነዳጅ እጥረት እና የትራንስፖርት ሁኔታ መራዘም የራሱ የሆነ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ተመራማሪው ተናግረዋል ።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ 42 በመቶ የመድሀኒት ፍላጎቷን በሀገር ውስጥ ባሉ የመድሀኒት ፋብሪካዎች ውየሸፈነች እንደሆነ የጤና ጥበቃ ሚንስቴር አስታውቋል።
የማህጸን እና ጡት ካንሰር አይነቶች በኢትዮጵያ ከሚታዩ ገዳይ የካንሰር አይነቶች ውስጥ ቀዳሚዎቹ ናቸው።
በተለይም ታማሚዎች ዘግይተው ወደ ህክምና መምጣታቸው በካንሰር የሚሞቱ ዜጎች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉ ተገልጿል።