የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ባለፉት 60 ዓመታት ቢያንስ 60 ሠራተኞቹን በሥራ ላይ እያሉ ህይወታቸውን እንዳጡ ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ባለፉት 6 አሥርት ዓመታት የዱር እንስሳትን እና የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ ሂደት ውስጥ ቢያንስ 60 ሠራተኞቹ በሥራ ላይ እያሉ ሕይወታቸውን ማጣታቸውን አስታውቋል።
ባለሥልጣኑ ዛሬ መጋቢት 1 ቀን 2018 ዓ.ም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የ60ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን የፊታችን መጋቢት 3 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚያከብር አስታውቋል።
የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ፣ ሠራተኞቹ ሕይወታቸውን ያጡት ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ጋር በተያያዙ የተለያዩ የሥራ ላይ ፈተናዎች መሆኑን ገልጸዋል።
ባለሥልጣኑ ባለፉት 60 ዓመታት ውስጥ ከ1 ሺህ 700 በላይ ለሚሆኑ ልዩ ልዩ የዱር እንስሳት ዝርያዎች ጥበቃ ማድረጉን ዋና ዳይሬክተሩ በመግለጫቸው ጠቁመዋል። በዚህም 14 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ የተፈጥሮ አካባቢ በጥበቃ ሥር እንዲውል መደረጉን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በሀገሪቱ ያለው አጠቃላይ የደን ሽፋን መጠን በአሁኑ ወቅት 23.6 በመቶ ለመድረሱ የተቋማቸው ስራ ውጤት እንዳለበት ገልጸው የደን ሽፋኑ መጨመር ለዱር እንስሳት ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ኃላፊው አክለዋል።
የባለሥልጣኑ 60ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል መከበር ለዱር እንስሳት ጥበቃ መሥዋዕትነት የከፈሉ ሠራተኞችን ለማሰብና የቀጣይ የጥበቃ ሥራዎችን አቅጣጫ ለመጠቆም ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።
ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶች እንዳሉ ቢጠቀስም፣ ሕገ-ወጥ አደን እና የሰዎች ህገወጥ መስፋፋት አሁንም ለዱር እንስሳት ጥበቃ ሥራ ዋነኛ ችግሮች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
ጥቁር ዳልጋ ያለው አንበሳ እና ዋልያ የተሰኙት ዱር እንስሳት በኢትዮጵያ የመጥፋት አደጋ ከተጋረጠባቸው እንስት መካከል ዋነኞቹ ናቸው።