የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር እንዳስታወቀው ኤርትራ ባለፉት ቀናት አዲስ ወታደሮችን ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን አስታውቋልል።
ሚንስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ለኤርትራ አቻቸው ኦስማን ሳሌህ በጻፉት ደብዳቤ የኤርትራ ጦር ከአማጺያን ጋር በመተባበር በሰሜን ምስራቅ በኩል ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን አስታውቋል።
ወደ ኢትዮጵያ የገቡት የኤርትራ ወታደሮችም ከአማጺያን ጋር በመቀናጀት ወታደራዊ እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሆኑም ተገልጿል።
በመሆኑም እነዚህ የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ባስቸኳይ እንዲወጡም ጠይቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ በደብዳቤው ላይ ከኤርትራ ጋር የገቡበትን አለመግባባት በዲፕሎማሲ ለመፍታት ዝግጁ እንደሆነም ገልጿል።
ሚንስትሩ አክለውም በተለይ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት እና የአሰብ ወደብን ለማግኘት ያቀረበቻቸውን ጥያቄዎች ጨምሮ ሌሎች ፍላጎቶችን ሁለቱን ሀገራት ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ለመወያየት ዝግጁ እንደሆነችም ተጠቅሷል።
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ባሳለፍነው ሳምንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት ኤርትራ በትግራይ ክልል “ጭፍጨፋ” ፈጽመዋል ማለታቸው ይታወሳል።
እንዲሁም የኤርትራ ጦር በኢትዮጵያ የትጥቅ ትግል የሚያካሂዱ ታጣቂዎችን የሎጅስቲክስ ድጋፍ እያደረገች እንደሆነም ጠቅላይ ሚንስትሩ ገልጸዋል።
ኤርትራ ለጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ አስተያየት በሰጠችው ምላሽ ኢትዮጵያ የባህር በር ይገባኛል በሚል ሊያካሂደው ላሰበው ወታደራዊ ጥቃት ለመሰንዘር ምክንያት እያስቀመጠ እንደሆነ አስታውቃለች።
ለሁለት ዓመት በዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ኤርትራ ከፌደራል መንግሥቱ ጎን በመሆን የትግራይ ሀይሎችን ስታጠቃ መቆየቷ ይታወሳል።
ይህ ጦርነት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በፌደራል መንግሥት እና ህወሀት መካከል የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ቆሟል።
ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ኤርትራ ግንኙነታቸው እየሻከረ የመጣ ሲሆን ህወሀት እና ኤርትራ ደግሞ አዲስ ወዳጅነት መመስረታቸው ይገለጿል።