የፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸምን የሚከታተለው የባለሙያዎች ቡድን መቐለ ገባ

ለሁለት ዓመት የዘለቀውን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እንዲቆም ምክንያት የሆነው የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት አፈጻጸም የሚከታተል የባለሙያዎች ቡድን ትግራይ ክልል መቐለ መግባቱ ተገልጿል።

ስምምነቱ እንዲፈረም ያደራደረው የአፍሪካ ህብረት የባለሙያዎችን ቡድን ያቋቋመው ከኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጀሪያ እና አልጀሪያ የተውጣጡ ናቸው።

ይህ የባለሙያዎች ቡድን በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት ታጣቂዎች ትጥቅ መፍታታቸውን፣ መሰረታዊ አገልግሎቶች መቀጠላቸውን፣ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀድሞ ቀዬአቸው መመለሳቸውን የመከታተል ሀላፊነት ተሰጥቶታል።

ዛሬ መቐለ መድረሱ የተገለጸው ይህ የባለሙያዎች ቡድን መቀመጫውን መቐለ በማድረግ የስምምነቱን አፈጻጸም ሲከታተል የቆየ ሲሆን ላለፉት ወራት በዕረፍት ላይ መቆየቱን የትግራይ ሰላምና ደህንነት ቢሮ አስታውቋል።

ይህ የባለሙያዎች ቡድን ከአስተዳድራዊ ዕረፍት በኋላ ወደ መቐለ የተመለሰው በአማራ እና ትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ ከሚነሳባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው ጠለምት በትግራይ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሰራዊት መካከል ግጭት በተከሰተ በሳምንቱ ነው።

ግጭቱን ተከትሎ ከአዲስ አበባ ወደ ትግራይ ከተሞች የደርሶ መልስ በረራዎች እንዲቆሙ አድርጓል።

ግጭቱ መቆሙን ተከትሎም በረራዎቹ ከአምስት ቀናት በኋላ ዳግም የቀጠሉ ሲሆን በራያ እና አላማጣ ከተሞች ግን ከስፍራው የለቀቀው እና አካባቢውን ሲያስተዳድር የነበረው የፌደራል ኮማንድ ፖስት እስካሁን አልተመለሰም።

ለደህንነታቸው ሰግተው ከራያ እና አካባቢው የተፈናቀሉ ዜጎችን እስካሁን ወደ ቤታቸው አልተመለሱም።

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በትናንትናው ዕለት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ የወልቃይት ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ መኖሪያ ቤታቸው ያልተመለሱት በህወሀት የፖለቲካ መያዣ በመደረጋቸው መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *