ፓርላማው የሞርጌጅ ባንክ ዳግም እንዲቋቋም ጠየቀ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሞርጌጅ ባንክ ወይም የቤት ብድር ባንክን ሀላፊነት ወስዶ መልሶ እንዲያደራጅ ጠይቋል፡፡

በሀገሪቱ ቀድሞ የነበረዉ የሞርጌጅ ባንክ ባልታወቀ ምክንያት ወደ ንግድ ባንክ መቀላቀሉ ስህተት መሆኑ ተገልጿል።

ፓርላመው ይህን የተጠየቀዉ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴርን የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በገመገመበት ወቅት ነው።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ፣ መሠረተ-ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ መሃመድ አብዶ በግምገማዉ ወቅት መንግስት በቤቶች ልማት ላይ ያለውን የፋይናንስ ችግር ለመፍታት የሞርጌጅ ባንክ መልሶ ማደራጀት አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ቀደም ባሉት ዘመናት የቤት ብድር ባንክ ሞርጌጅ እንደነበረና ባልታወቀ ምክንያት ፈርሶ ወደ ንግድ ባንክ የተቀላቀለ መሆኑን የቋሚ ኮሚቴዉ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር እሸቱ ተመስገን ተናግረዋል።

የዜጎችን የቤት ችግር ለማቃለል የታቀደውን የቤቶች ልማት ለማከናወን አንዱ ተግዳሮት በቤት ልማት ላይ ያለው የፋይናንስ አቅርቦት ውስንነት መሆኑን በግምገማው ወቅት ተገልፆል።

የቋሚ ኮማቴዉ ሰብሳቢ መሀመድ የመኖሪያ ቤት ችግርን ሙሉ በሙሉ መፍታት ባይቻልም በሌሎች ሀገራትም ችግሩን ለመፍታት ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች አንዱ የቤት ብድር ባንክ አገልግሎት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ስለሆነም መንግስት አዲስ ከማዋቀር ይልቅ የነበረውን የኮንስትራክሽን ባንክ መልሶ ማደራጀት እንዳለበት አሳስበዋል።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ኃላፊነቱን ወስዶ ይህንን ባንክ መልሶ እንዲደራጅም ማሳሰቢያ ሰጥተዋል
‎አያይዘውም ዜጎች ተደራጅተው በረጅም ጊዜ ክፍያ የቤት ባለቤት ሊሆኑ የሚችሉበት የባንክ አገልግሎት በመሆኑ ስርአቱ መዘርጋት እንዳለበት አክለዋል።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሣኒ የሞርጌጅ ስርዓት እንዲዘረጋ የምክር ቤቱና የቋሚ ኮሚቴው ክትትልና ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ አሁን ላይ በብቸኝነት ያለው የሞርጌጅ ባንክ ጎህ የቤቶች ባንክ ሲሆን በሀገሪቱ ካለው የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ጋር ሲነጻጸር አጥጋቢ እንዳልሆነ ይገለጻል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከወራት በፊት በቀጣዮቹ ዓመታት ውስጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ 1 ነትብ 5 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት እቅድ መያዙን መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ቤቶቹ በምን መንገድ እና በማን ወጪ እንደሚገነቡ ያልጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በመንገስት እና በግል ኩባንያዎች አማካኝነት የተገነቡ ቤቶች 350 ሺህ ያህል ብቻ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ በየዓመቱ ከ1 ሚሊዮን በላይ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ያለ ሲሆን አሁን ላይ 100 ሺህ ቤቶችን በአንድ ዓመት ውስጥ ለመገንባት በግል እና በመንግስት አጋርነት በመገንባት ላይ ናቸው ተብሏል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከአንድ ወር በፊት አዲስ የቤት ፖሊሲን ያጸደቀ ሲሆን ፖሊሲው በከተሞች እና በገጠር አካባቢ የመኖሪያ ቤቶችን በፍላጎቱ ልክ መገንባት የሚቻልባቸውን መፍትሔዎች በሚያስቀምጥ መልኩ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *