ኦሪጅናል ቴፍ-ሊ የተባለው ከጤፍ የተሰራ የወተት ምርት ዛሬ በለንደን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና በአምራቾቹ ትብብር በተዘጋጀ የማስተዋወቂያ መድረክ ላይ ይፋ ተደርጓል፡፡
በዝግጅቱ ላይ ከንግድ ማህበረሰቡ፣ ከሚዲያ፣ ከእንስሳት ተዋጽኦዎች ነፃ በሆኑ ምግቦች ምርት እና ግብይት ውስጥ የሚሳተፉ ኢንዱስትሪዎች አባላት እና የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ተገኝተዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ከእፅዋት የተዘጋጁ የምግብ አማራጮች ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱ የሚታወቅ ሲሆን ዝግጅቱ ጤፍን ለአለም አቀፍ ታዳሚዎች የበለጠ ለማስተዋወቅ እድል ፈጥሯል።
በብሪታንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብሩክ መኮንን በመክፈቻ ንግግራቸው ጤፍ በኢትዮጵያዊያን የአመጋገብ ዘይቤ ውስጥ ያለውን ሰፊ ቦታ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም በሚችሉ የምግብ ስርዓቶች ጥናቶች ላይ ሊያበረክት ስለሚችለው አዎንታዊ አስተዋጽኦ አብራርተዋል፡፡
የኦሪጅናል ቴፍ-ሊ (The Original Teff-ly) መስራቾች አዲሱ ምርት አዳዲስ የገበያ ሰንሰለቶችን ከመፍጠር በተጨማሪ ጤፍ ከኢትዮጵያ ጋር የተቆራኘ መሆኑን ለአለም እንደሚያስተዋውቅ ተናግረዋል።
ምርቱ በአሁኑ ጊዜ በዩናይትድ ኪንግደም በመመረት ላይ የሚገኝ ቢሆንም፣ በቀጣይ የምርት ሂደቱን ወደ ኢትዮጵያ ለማሸጋገር እንዲሁም የሥራ ዕድልን በማስፋፋት እና በጤፍ ምርት ላይ እሴት በመጨመር በተሻለ ዋጋ ለኤክስፖርት ገበያ የማቅረብ እቅድ እንዳለም ታውቋል፡፡
ባህላዊ እውቀትና ዘመናዊ የምግብ ቴክኖሎጂን በማጣመር አዳዲስ ምርቶችን ለአለም ዓቀፍ ሸማቾች እንዴት ማቅረብ እንደሚቻል በታየበት ዝግጅት ላይ እንግዶች የምርት ቅምሻ አድርገዋል።
ዝግጅቱ የንግዱ ማህበረሰብ፣ የዳያስፖራ አባላት፣ የፈጠራ ባለሙያዎች እና የሶሻል ሚድያ ይዘት ፈጣሪዎች በጋራ የተገናኙበት መድረክ በመፍጠር ትውውቅ እና ትስስር እንዲካሄድ ያስቻለ ሲሆን ከምርት ማስጀመር ባሻገር፣ ቴፍሊ ወተትን ከዓለም አቀፍ ገበያዎች እና ከወደፊት የኢኮኖሚ እድሎች ጋር የሚያገናኝ ዝግጅት ሆኖ ተጠናቋል፡፡
ኢትዮጵያ ጤፍን በማብቀል እና የባለቤትነት መብትን የያዘች ሲሆን ምርቱ ዝቅተኛ የስኳር መጠን መያዙ ተወዳጅ አድርጎታል።