ኢትዮጵያዊ ባለፉት ስድስት ወራት እንደ ሀገር ከ704 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ እንደተቻለ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል።
አፈጻጸሙ በገቢዎች ሚኒስቴር በግማሽ ዓመቱ ለመሰብሰብ ከታቀደው 640 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ውስጥ 704 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 110 በመቶ ተሳክቷል ተብሏል።
ይህ ገቢ ባለፉት ጊዜያት ለዓመታት ሲሰበሰብ ከነበረው ገቢ ጋር የሚመሳሰል እንደሆነ ተገልጿል።
የተሰበሰበው ገቢ ከባለፈው ዓመት ስድስት ወራት አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር የ63 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው ሲሆን ስኬቱ ኢትዮጵያ የውስጥ አቅሟን በማጎልበት እያንሰራራች ለመሆኑ ሁነኛ ማሳያ ተድርጎ የሚወሰድ ነው ሲል መንግሥት አስታውቋል።
በግማሽ ዓመቱ ከሀገር ውስጥ ታክስ 362 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የተሰበሰበ ሲሆን ከውጪ ንግድ ቀረጥ እና ታክስ ከ341 ነጠብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ተስብስቧል።
ኢትዮጵያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ትሪሊዮን ብር ባሳለፍነው በጀት ዓመት ላይ መሰብሰቧ ይታወሳል።
በዘንድሮው በጀት ዓመት 1.5 ትሪሊዮን ብር ገቢ ከታክስ ለመሰብሰብ ማቀዷ ይታወሳል።
ይህ በዚህ እንዳለ የንግድ ስራ ፈቃድ እድሳት ማብቂያ ቀን መራዘሙ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ የዓመታዊ ንግድ ፈቃድ እድሳት ከሀምሌ 1 እስከ ታህሳስ 30 ቀን ድረስ ያለቅጣት የሚታደስበት ጊዜ ነው።
አመታዊው የንግድ ፈቃድ እድሳት ያለቅጣት የሚታደስበት ጊዜ በትላንትናው ዕለት ታህሳስ 30/2018 ዓም ያበቃ ሲሆን የማደሻ ጊዜው ለተጨማሪ 15 ቀናት መራዘሙን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አሳውቋል።
እንደ ንግድ ቢሮው መረጃ እስከ ማክሰኞ ታህሳስ 28/2018 ዓ/ም ባለው መረጃ 230 ሺ የሚሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት እድሳት ማከናወናቸውን አሳውቋል።
የንግድ ስራ ፈቃድ እድሳት አገልግሎት ከሠኞ-ቅዳሜ ከጠዋቱ 2፡30 እስከ ምሽቱ 2፡30 በኦንላይን እየተሠጠ የሚገኝ ሲሆን በቀሩት ቀናት ንግድ ፈቃዳቸውን ያላሳደሱ ነጋዴዎች እንዲያሳድሱ ቢሮው አሳስቧል።