የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ከ2 ቢሊዮን በላይ ብር አረቦን ሰበሰበ

ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ 2 ነጥብ 08 ቢሊዮን አረቦን ብር መሰብሰቡን የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ገለጸ።

መድን ፈንዱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከተው፤ በመጀመሪያ ሩብ ዓመት ውስጥ 2 ነጥብ 08 ቢሊዮን አረቦን ብር እንደሰበሰበና ይህም ከታቀደው እቅድ አንጻር መቶ በመቶ ተፈጻሚ ሆኗል።

ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲታይም የ27 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተገልጿል። የተሰበሰበው አረቦን ብር ሊያድግ የቻለው የአባል ፋይናንስ ተቋማት ተቀማጭ ገንዘብ በማደጉ ምክንያት እንደሆነም ተጠቅሷል።

በ2018 በጀት ዓመት በአጠቃላይ ብር 9 ነጥብ 56 ቢሊዮን ከአባል ፋይናንስ ተቋማት ለመሰብሰብ ዕቅድ ይዞ እየሠራ እንደሚገኝና ይህም ከ2017 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ30 ነጥብ 25 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ እስከ አሁን ባከናወናቸው ተግባራት 16 ቢሊዮን የአረቦን ብር መሰብሰቡን ገልጾ፤ ከዚህም ውስጥ 14 ነጥብ 51 ቢሊዮን ብር ከመደበኛ ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰቡን እና 1 ነጥብ 42 ቢሊዮን ብር ከወለድ ነጻ ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰቡን አስታውቋል።

ከተሰበሰበው አጠቃላይ የአረቦን ብር ውስጥ 8 ቢሊዮን ብር ከግል ባንኮች፣ 7 ነጥብ 74 ቢሊዮን ብር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም 186 ነጥብ 62 ሚሊዮን ብር ከማክሮ ፋይናንስ ተቋማት የተገኘ መሆኑ ተመላክቷል።

ከኢንቨስትመንት አንጻርም መድን ፈንዱ በ2018 በጀት ዓመት መጀመሪያ ሩብ ዓመት 1 ነጥብ 82 ቢሊዮን ብር በመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ ላይ ኢንቨስት እንዳደረገና 190 ሚሊዮን ብር በሙዳራባህ የቁጠባ ኢንቨስትመንት ሂሳብ እንዳስቀመጠ መድን ፈንዱ አስታውቋል።

በዚህም መሠረት አጠቃላይ የመድን ፈንዱ ኢንቨስትመንት 16 ነጥብ 49 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ እና ከዚህም 15 ነጥብ 05 ቢሊዮን ብር በመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ ላይ ኢንቨስት የተደረገ መሆኑን ገልጿል።

ቀሪው 1 ነጥብ 44 ቢሊዮን ብር በሙዳራባህ የቁጠባ ኢንቨስትመንት ሂሳብ ስለመቀመጡም ተገልጿል። ፈንዱ እስከ አሁን 1 ነጥብ 85 ቢሊዮን ብር ከኢንቨስትመንት ሥራው ገቢ ያገኘ ሲሆን፤ በ2018 በጀት ዓመት ብር 3 ነጥብ 02 ቢሊዮን ገቢ ለማግኘት እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ዋነኛ ዓላማ በባንክና በማይክሮፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የተቀማጭ ገንዘብ ላስቀመጡ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች የኢንሹራንስ ሽፋን በመስጠት ለገንዘብ አስቀማጮቹ ጥበቃ ማድረግ እና ለፋይናንስ ሥርዓት መረጋጋት አስተዋጽኦ ማበርከት መሆኑ በመግለጫው አመልክቷል።

በዚህም መሠረት አንድ የፋይናንስ ተቋም ኪሳራ ላይ ቢወድቅ ፈንዱ ለእያንዳንዱ ገንዘብ አስቀማጮች እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር ወዲያው ተመላሽ ያደርጋል።

ፈንዱ የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ ለመወጣት የሚያስችለውን የገንዘብ አቅም ለመገንባት አረቦን የሚባል ፋይናንስ ተቋማት ያሰባስባል፤ ይበልጥ ገቢውን ለማሳደግም የተሰበሰበውን አረቦን መልሶ ኢንቨስት ያደርጋል።

የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 482/2013 -1 የተቋቋመ ሲሆን፤ ሥራውን በይፋ ከጀመረ ከሁለት ዓመት በላይ አስቆጥሯል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *