በአፋር ክልል በተፈጠረ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ከ43 ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናቀሉ

በአፋር ክልል፣ ኪልበቲ ረሱ ዞን፣ በርሃሌ ወረዳ ባሳለፍነው ቅዳሜ ምሽት በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ 43,456 ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸው ተገልጿል፡፡

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ሁሴን እንዳሉት ለተፈናቃዮቹ የሚሆን ምግብ እና መጠለያ፤ ከባድ ጉዳት ወደ ደረሰባቸው ቀበሌዎች እየተጓጓዘ ነው ብለዋል። 

በክልሉ ባሳለፍነው ቅዳሜ ጥቅምት 1 ቀን 2018 ዓ.ም ምሽቱ አንድ ሰዓት አካባቢ የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ፤ ከበርሃሌ በተጨማሪ በተመሳሳይ ዞን ውስጥ በሚገኙት ኮናባ እና ዳሎል ወረዳዎችም የተከሰተ እንደነበርም የክሉ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ባወጣው መግለጫ ላይ ጠቅሷል።

በበርሃሌ ወረዳ የመጀመሪያው ርዕደ መሬት ከደረሰበት ከምሽት 12 ሰዓት ጀምሮ ለስድስት ጊዜያት ያህል የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን አቶ አሊ አስረድተዋል። 

በወረዳው ካሉ ቀበሌዎች በርዕደ መሬቱ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው፤ ቡሬ እና አስ ጉቢ አላ ቀበሌዎች መሆናቸውን ዋናው አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

በአደጋው ሳቢያ በቀበሌዎቹ ነዋሪ የሆኑ ስድስት ሰዎች መጎዳታቸውን እንዲሁም አንድ የ12 ዓመት አዳጊ ልጅ ህይወት ማለፉንም ገልጸዋል።

ከተጎጂዎቹ ውስጥ ሶስቱ ወደ በርሃሌ ሪፈራል ሆስፒታል ተወስደው ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን አቶ አሊ አመልክተዋል።

በሁለቱ ቀበሌዎች የቤቶች መፍረስን ያስከተለው ርዕደ መሬት በተከሰተበት ወቅት አብዛኞቹ ነዋሪዎች ከቤት ውጭ የነበሩ በመሆኑ የተጎጂዎች ቁጥር ሊቀንስ መቻሉንም አብራርተዋል።

በቡሬ እና አስ ጉቢ አላ ቀበሌዎች ያሉ በርካታ ቤቶችን ያፈረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ የደረሰው፤ ቅዳሜ ዕለት ምሽት 1:18 ደቂቃ ላይ ነበር። በሬክተር ስኬል 5.6 በተለካው በዚህ ርዕደ መሬት ከ43 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶች እንደፈረሱም ተናግረዋል።  

የአፋር ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ባወጣው መግለጫ፤ በመሬት መንቀጥቀጡ “በርካታ የመኖሪያ ቤቶች እና የመንግስት መዋቅሮች ሙሉ በሙሉ በመፍረሳቸው ከፍተኛ የሆነ የንብረት ውድመት ደርሷል” ብሏል።

የበርሃሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ በበኩላቸው በመኖሪያ ቤቶች እና በንብረት ላይ የደረሰው የጉዳት መጠን ለማጣራት አንድ የጥናት ቡድን ወደ ቀበሌዎቹ መላኩን አስረድተዋል።

በሁለቱ ቀበሌዎች ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው እና የተፈናቀሉ ሰዎች ብዛት 43,456 መሆኑን የገለጹት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ፤ ተፈናቃዮቹን ለመርዳት “ኮማንድ ፖስት” ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

በአፋር ክልል በአዋሽ አካባቢ ባሉ ቦታዎች ባለፈው ዓመት ባጋጠሙ ተመሳሳይ የመሬት መንቀጥቀጦች ከ85 ሺህ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ይታወሳል።

ይህ በዚህ እንዳለም ባሳለፍነው ቅዳሜ ዕለት በትግራይ ክልል ተመሳሳይ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች የተከሰቱ ሲሆን የመንቀጥቀጥ አደጋው መቀሌን ጨምሮ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ተሰምቷል፡፡

እስካሁን ባለው መረጃ ስድስት መኖሪያ ቤቶች በአደጋው ምክንያት እንደወደሙም ተገልጿል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *