በኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን በፋይናንስ ለመደገፍ ‘ኢንተርፕርነርሺፕ ኢንቨስትመንት ባንክ’ ሊቋቋም መሆኑ ተገልጿል።
ባንኩ በ20 ሚሊዮን ዶላር መነሻ ካፒታል የሚመሰረት ሲሆን፣ ወጣቶች ለድጋፍ የሚያስይዙት ዋስትና የፈጠራ ሀሳባቸውን ብቻ እንደሚሆን ተጠቁሟል።
ባንኩን ለማቋቋም የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት በሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል እና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ ፊርማ የተረጋገጠ ሲሆን፣ ተቋሙ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለኢንተርፕራይዞች አቅም መጎልበት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ተገልጿል።
ይህ እርምጃ መንግስት የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያወጣቸውን ፖሊሲዎች ወደ ተግባር የመቀየር አካል መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ገልጸው፣ ባንኩ የወጣቶችን ጥያቄ በመመለስ የፈጠራ አቅማቸውን ለማጎልበት ያስችላል ብለዋል።
ከመነሻ ካፒታሉ 10 ሚሊዮን ዶላር ከአፍሪካ ልማት ባንክ በድጋፍ የተገኘ ሲሆን፣ ቀሪው በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እንደሚሸፈን ታውቋል።
ባንኩ ራሱን ችሎ የሚቋቋም ሲሆን፣ በቀጣይም ወጣቶች በካፒታል ገበያ ላይ በብዛት የሚሳተፉበትን ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።
በኢትዮጵያ ካለው ጠቅላላ ህዝብ ውስጥ 70 በመቶ ያህሉ እድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች እንደሆነ የብሔራዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ሪፖርት ያሳያል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ10 ሚሊዮን በላይ ስራ አጥ ወጣቶች ያሉ ሲሆን በየዓመቱም ከሶስት ሚሊዮን በላይ ወጣቶች የስራ ዓለሙን ይቀላቀላሉ።
የአየር ንብረት ለውጥ፣ ግጭቶች፣ የኑሮ ውድነት እና ሌሎች የኢኮኖሚ ችግሮች የወጣቶችን ስራ እድል እየተፈታተኑ ያሉ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው።
ወጣቶች የስራ እድል በሀገር ውስጥ ባለማግኘታቸው ምክንያት በየ ዓመቱ ከ200 ሺህ በላይ ዜጎች በህገወጥ መንገድ ወደ መካከለኛው ምስራቅ እና ሌሎች ሀገራት እንደሚሰደዱ የአይኦኤም ሪፖርት ያስረዳል።