ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ የጉምሩክ ቀረጥና ተጨማሪ ቀረጥ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት አንጻር በግማሽ መቀነሱ ተገለጸ። ይህ ቅናሽ በዋናነት ከውጭ የሚገቡ የሸቀጦች መጠን እና ዋጋ በመቀነሱ ምክንያት እንደሆነ ተጠቁሟል።
እኤአ 2015/16 ጀምሮ የነበረው የጉምሩክ ቀረጥና ተጨማሪ ቀረጥ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 2.1% የነበረ ሲሆን፣ ይህ አሃዝ በ2022/23 ወደ 1.0% ዝቅ ብሏል።
የዚህ መቀነስ ዋነኛ ምክንያት፣ ከውጭ የሚገቡ የሸቀጦች መጠን ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ከ24% ወደ 10% በመውረዱ እንደሆነ የገንዘብ ሚኒስቴር የሰሞኑን ጥናት ያመለክታል።
ይህ የገቢ ቅናሽ አጠቃላይ የግብር እና የሀገር ውስጥ ምርት ጥምርታ መውረድ ውስጥ አንድ አራተኛውን ይዟል።
ከ2015/16 እስከ 2021/22 ባለው ጊዜ ውስጥ፣ የውጭ ምርቶች መጠን መቀነስ በዋነኝነት በካፒታል ዕቃዎችና በኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃዎች ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በመቀነሱ ምክንያት ነው።
ሚኒስትሩ ከዓለም አቀፉ ፊስካል ጥናት ተቋም (IFS) በጋራ ባዘጋጁት አዲስ ጥናት ላይ እንደገለፁት የውጭ ምንዛሪ እጥረት የውጭ ምርቶች ፍላጎትን በመቀነስ ለዚህ ለውጥ አስተዋጽኦ አድርጓል።
በ2021/22 እና በ2022/23 መካከል የውጭ ምርቶች እና የሀገር ውስጥ ምርት ጥምርታ መቀነስ በአብዛኛው በዋጋ ለውጦች ምክንያት መሆኑን ሪፖርቱ አክሎ ገልጿል።
የኢንዱስትሪዎች የሀገር ውስጥ ገበያ ድርሻ 41 በመቶ መድረሱን የኢንዱስት ሚኒስቴር ከወራት በፊት መግለጹ ይታወሳል፡፡
ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በ3ኛው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ዙሪያ በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳሉት የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች የሀገር ውስጥ ገበያ ድርሻ በ2013 ዓ.ም ከነበረበት የ30 በመቶ አሁን ላይ ወደ 41 በመቶ አድጓል ብለዋል፡፡
የኢንዱስትሪዎች ምርት የገበያ ድርሻን እ.ኤ.አ. በ2030 ወደ 65 በመቶ የማድረስ እቅድ ተይዟል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም የሀገር ውስጥ ምርቶችን ለማበረታት የተለያዩ እቅዶች ተቀርጸው እየተተገበሩ መሆኑን ተናግረው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ቀስ በቀስ በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት፣ በሀገር ውስጥ ለሚመረቱ ምርቶች የገበያ እድሎችን መፍጠር እና ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሄዎችን መፈለግ የሚያስችሉ ፖሊሲዎች ተቀርጸዋልም ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት ከውጭ ሀገራት ተገዝተው ይገቡ ከነበሩ ምርቶች መካከል 96 የምርት አይነቶችን በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ በማድረግ በ2014 ዓ.ም 318 ሚሊዮን ዶላር ማዳን መቻሉን አቶ መላኩ በመግለጫው ላይ ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም ባለፉት ዘጠን ወራት ውስጥ ደግሞ በሀገር ውስጥ በተመረቱ ተኪ ምርቶች ምክንያት 3.1 ቢሊዮን ዶላር ማዳን መቻሉን ገልጸዋል፡፡ በሀገር ውስጥ ተኪ ምርቶች መጨመር ምክንያትም በኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ንግድ ሚዛን ላይ የ10 በመቶ እድገት እንዲመዘገብ አስተዋጽኦ ማድረጉን ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡
ህዝቡ የሀገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ባህሉ እየተሻሻለ መምጣቱ፡፡ የኢንዱስትሪዎች ምርቶች ጥራት እያደገ መምጣት፣ የግዢ መመሪያ መሻሻል እና ሌሎች የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሁኔታዎች የሀገር ውስጥ ምርቶች የገበያ ድርሻ እንዲያድግ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡
በቀጣይም 83 ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ወደ ጎረቤት ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ገበያዎች ላይ ለማቅረብ እቅድ መያዙን የተናገሩት አቶ መላኩ በተለይም ወታደራዊ አልባሳትና የቢራ ብቅል ምርቶችን መላክ ተጀምሯልም ብለዋል፡፡