ሩሲያ ለኢትዮጵያ ባህር ሀይል ድጋፍ እያደረገች መሆኑ ተገለጸ

ኢትዮጵያ በሩሲያ ድጋፍ እያከናወነችው የሚገኘው የባህር ኃይል ዋና መስሪያ ቤት ሕንጻ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ነው ተብሏል።

ኢትዮጵያ በሩሲያ ድጋፍ በአዲስ አበባ ከተማ ጃንሜዳ አካባቢ እያከናወነችው የሚገኘው የባህር ኃይል ዋና መስሪያ ቤት ሕንጻ ግንባታ 95 በመቶ መጠናቀቁ ተነግሯል።

በሦስት ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው የባህር ኃይል ዋና መስሪያ ቤት ባለ አራት ፎቅ ሕንጻ ሲሆን፤ የአስተዳደር ቢሮዎች፣ የሕክምና ክሊኒክ፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ያካተተ ስለመሆኑ ስፑትኒክ አፍሪካ ዘግቧል።

ይህም ፕሮጀክት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ቀጣናዊ ተጽዕኖ መልሳ ለማግኘት የምትከተለው ሰፊ ስትራቴጂ አካል ነው የተባለ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ በታቀደለት ጊዜ በቅርቡ እንደሚጠናቀቅም ተነግሯል።

በተያዘው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ኢትዮጵያ የባህር ኃይል ልማትና ስልጠናን ለመደገፍ ኢትዮጵያ ከሩሲያ የትብብር ስምምነት የተፈራረመች ሲሆን፤ ስምምነቱም ከፈረንሳይ ጋር ቀደም ሲል የተደረገው የባህር ኃይል አጋርነት መቋረጡን ተከትሎ የተደረገ ነው።

በወቅቱም የሩሲያ ባሕር ኃይል ምክትል አዛዥ አድሚራል ቪላዲሚር ቮሮቢቭ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል የሚገነባቸውን የባሕር ኃይል ተቋማት ጠቅላይ መምሪያውና በቢሾፍቱ የሚገኘውን ማሰልጠኛ ማዕከል የጎበኙ ሲሆን፤ ከጉብኝታቸው በኋላም ሞስኮ የሰው ሀይል ለማሰልጠን እና የኢትዮጵያን የባህር ሀይል አቅም በማሳደግ ድጋፍ እንደምታደርግ ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡

በሩሲያ ድጋፍ በአዲስ አበባ እየተከናወነ የሚገኘው የባህር ኃይል ዋና መስሪያ ቤቱ ግንባታ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ የባህር በር የሌላት ሆና ለቆየችው ኢትዮጵያ፤ ብሔራዊ የባህር ኃይልን መልሶ ለማቋቋም ባላት ዓላማ ውስጥ ትልቅ እርምጃ ነው ስለመባሉም ዘገባው አመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያ ከአውሮፓውያኑ 1993 አንስቶ ወደብ አልባ ሀገር ብትሆንም፤ መንግሥት የባህር ኃይል አቅሞች የንግድ መስመሮችን ለመጠበቅ፣ ለዓለም አቀፍ የባህር ላይ ስጋቶች ምላሽ ለመስጠት እና ዓለም አቀፍ የውሃ አቅርቦትን በጅቡቲ እና በሱዳን ወደቦች በኩል ለማድረስ ወሳኝ ስለመሆኑን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ብቁና የሰለጠነ የባህር ሃይል ለሀገር ደህንነት እና ለክልላዊ መረጋጋት ወሳኝ መሆኑን በማንሳት፤ በአዲስ መልክ በባህር ኃይል አደረጃጀት እና በባህር በር ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ እንደሚገኝ መግለጹ ይታወቃል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *