ጤናማና ዘላቂ የአመጋገብ ሥርዓትን ለማበጀት ያቀደ ”ኢኮ ፉድ ሲስተም” የተሰኘ ፕሮግራም ይፋ ተደረገ

ፕሮግራሙ በአዲስ አበባ ያለውን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዲሁም ሰዎችን ላላስፈላጊ ውፍረት የሚዳርገውን ከመጠን በላይ የሆነ የአመጋገብ ሥርዓትን የሚያጠና ነው ተብሎለታል።

በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸው ተፅዕኖዎችን እና የተለያዩ ችግሮችን መቋቋም የሚችሉ የምግብ ስርዓትን ለማቅረብ ያለመ መሆኑ የተነገረለት ይህ ፕሮግራም የአዲስ አበባ ነዋሪን በቀጥታ ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል።

ፕሮግራሙ በከተሞች ላይ ያለው የስርዓተ ምግብ ምን ሁኔታ ላይ ነው፣ ምንስ መስተካከል አለበት የሚሉ እና ሌሎች ጥናቶችም እየከወነ ለፖሊሲ አውጭዎች እና ለሚመለከታቸው ተቋማት መረጃ የመስጠት ስራ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ይሰራል ተብሏል።

በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት የስነ ምግብ እና የአካባቢ ጤና ዳይሬክተር ዶክተር ማስረሻ ተሰማ እንዳሉት ፕሮጀክቱ በከተማዎች ላይ ያለን የስርአተ ምግብ ሁኔታን እየተከታተሉ መረጃ መሰብሰብ ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ስርዓተ ምግብ ምን ደረጃ ላይ ነው፣ ምንስ ሊስተካከል ይገባል የሚሉና ተያያዥ ሀሳቦች ላይ ጥናት እንደሚከናወንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ የምግብ ስርዓት ውስጥ ያለውን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በዘላቂነት ለመፍታት ይሰራል የተባለለት ይህ ፕሮጀክት ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በአጋርነት የሚከወን እና በጋልዌይ ዩኒቨርሲቲ የሚመራ መሆኑን ሰምተናል።

ፕሮጀክቱ በአውሮፓ ህብረት እና በአለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ የገንዘብ ደጋፍ የተደረገለት መሆኑ የተነገረ ሲሆን በተለይ በአዲስ አበባ ጤናማ፣ ዘላቂ እና በተመጣጣኝ ዋጋ ሊገኙ የሚችሉ ምግቦች አቅርቦት ዙሪያ ለመስራት አቅዷል።

ፕሮጀክቱ ወደ ተግባር ሲገባም በአዲስ አበባ እየታየ ያለውን የስርዓተ ምግብ መጓደል ያስተካክላል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ሲሆን በቀጣዮቹ አመታትም ወደ ሌሎች ከተሞች የሚስፋፋ ነው ተብሏል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *