የኢትዮጵያ ጦር በአዲሱ የአፍሪካ ህብረት ሰላም ማስከበር ተልዕኮ እንዲሚሰማራ ተገለጸ

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የኢትዮጵያ ጦር በአዲሱ የአፍሪካ ህብረት ሰላም ማስከበር ተልዕኮ እንዲሳተፍ ተስማሙ፡፡

በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮ (አውሶም) ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንዲሰማራ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መስማማታቸው ተገልጿ፡፡

ከሁለት ቀናት በፊት ወደ ሶማሊያ ያቀኑት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ  ከሶማሊያ መከላከያ ሰራዊት አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ኦዳዋ ዩሱፍ ራጌ  ጋር ተገናኝተው በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

ስምምነቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃሙድ በቅርቡ በአዲስ አበባ ያደረጉትን የሁለትዮሽ ውይይት ተከትሎ የተደረገ የቴክኒክ ምክክር አካል ነው ተብሏል፡፡

የጦር መሪዎቹ የሞቃዲሾ ውይይት በቀጠናዊ ደህንነት፣ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምን እና መረጋጋትን የማስጠበቅ አስፈላጊነት ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑ ተዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን የወደብ የመግባብያ ስምምነትን ተከትሎ አዲስ አበባ እና ሞቃዲሾ በዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ውስጥ መክረማቸው ይታወሳል፡፡

የሀገራቱ መሪዎች በቱርክ ተገናኝተው ከመከሩ በኋላ በሁለቱ ሀገራቶች መዲና የተገናኙት የከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ልዑክ የሁለትዩሽ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

ከሁለት ቀናት በፊት በጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ የተመራው እና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ኃላፊ ሬድዋን ሁሴን እና ሌሎች ኃላፊዎችን ያካተተው ልዑክ፤ ከሶማሊያ መከላከያ ሰራዊት አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ኦዳዋ ዩሱፍ ራጌ እና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር አብዱላሂ መሐመድ አሊ ጋር ሰፊ ውይይት ማድረጉ ተነግሯል፡፡

በውይይቱ ሁለቱ አካላት በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮ (አውሶም) ስራዎች ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሚና እንዲኖረው መስማማታቸውን በጋራ መግለጫቸው አመላክተዋል፡፡

በባለ ስምንት ነጥብ የጋራ መግለጫው ላይ አልሸባብን ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት በበቂ ሁኔታ መደገፍ እንደሚያስፈልግ የጦር መሪዎቹ ገልጸው ሽብርተኝነትን ለመከላከል በጋራ ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት አጽንኦት ሰጥተዋል።

በተጨማሪም ሀገራቱ የህዝቦችን ሉዐላዊነት እና የግዛት አንድነት ለማክበር በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚደረግ ማንኛውም ግንኙነት በሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ በኩል ማለፍ እንደሚገባው ተስማምተዋል ነው የተባለው፡፡

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ባላት የሁለትዮሽ ስምምነት እስከ 7 ሺህ የሚሆኑ ወታደሮቿን በሀገሪቱ ማሰማራቷ ይታወሳል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *