መንግሥት የጎዳና ተዳዳሪዎችን በግዴታ ወደ ማጎሪያ ስፍራ እያስገባ መሆኑን ኢሰመኮ ገለጸ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጎዳና ላይ ያሉ ሰዎችን ያለፈቃዳቸው መያዝና ወደ ማቆያ ማዕከላት ማስገባት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ስለሚያስከትል ሊቆም ይገባል ሲል  አሳስቧል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በሚከበሩ ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት፣ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ጉባኤዎች እንዲሁም ከሌሎች ተመሳሳይ ኹነቶች ጋር በተያያዘ ውሎና አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ሰዎችን በኃይል በማንሳት በአንድ ስፍራ እንዲቆዩ የማድረግ ስራ በተደጋጋሚ እንደሚከናወን መግለጫው አመላክቷል፡፡

ኢሰመኮ በታኅሣሥ ወር 2017 ዓ.ም ባደረጋቸው ክትትሎች በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ “ቃሊቲ አካባቢ” ተብሎ በሚጠራው የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ አካባቢ ሰፊ መጋዘን ውስጥ ከጎዳና ላይ የተነሱ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

ወደ ማቆያው ከገቡት ሰዎች መካከል በማዕከሉ ከመቆየት እና የእርሻ ሥራ ከመሥራት እንዲመርጡ በማድረግ፤ የእርሻ ሥራ ለመሥራት የመረጡ ሰዎች በተለያዩ አካባቢዎች ወደሚገኙ እርሻ ጣቢያዎች ተወስደው እንዲሠሩ እንደሚደረግ ነው የተገለጸው፡፡

በዚህም ድርጊቱ የነጻነት መብታቸውን ጨምሮ ሌሎች መሠረታዊ የሰብአዊ መብቶቻቸውን የሚጥስ በመሆኑ ሊቆም እንደሚገባ ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡

ችግሩ የፖሊሲ መፍትሔ የሚያሻው ነው ያለው የኢሰመኮ ሪፖርት ወደመጡባቸው አካባቢዎች የመመለስ እና የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች ሰብአዊ መብቶቻቸውን ባከበረ መልኩ ማከናወን ሊደረግ እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡

ከዚህ ባለፈም በጊዜያዊ ማቆያ ማዕከሉ ከንጽሕና እና ከጤና አጠባበቅ ጋር በተያያዘ በሰዎች ሕይወትና ጤና ላይ አደጋ የሚጥሉ ሁኔታዎች እንዳይፈጠር፤ ከአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር ውይይቶችን በማድረግ ጉዳዩን በመከታተል ላይ እገኛለሁ ብሏል፡፡

የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ወደማቆያ በፈቃደኝነት ለሚገቡ ሰዎች የሚዘጋጁ የተሐድሶ ማዕከላት መሠረተ ልማት የተሟላላቸው፣ ንጽሕናቸው የተጠበቀ፣ ለደኅንነት እና ለጤና ሥጋት የማይፈጥሩ ተደርገው የተዘጋጁ መሆናቸው ሊረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።

መንግስት እስካሁን በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫ ያላወጣ ሲሆን የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ሌሎች ዓመታዊ ስብሰባዎች ሲካሄዱ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ስራ እንዳይሰሩ መከልከል የተለመደ ነው፡፡

ለአብነትም ባለፈው ዓመት በጎዳናዎች ዳር የሊስትሮ ስራ እና ሌሎች አነስተኛ ንግድ የሚሰሩ ዜጎችን የአፍሪካ ህበረት የመሪዎች ስብሰባ በሚካሄድበት ወቅት እንዳይሰሩ በጸጥታ ሀይሎች ተከልክለው ነበር፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *