ኢትዮጵያ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ እንዳይሰጥ አገደች

በዩንቨርሲቲዎች የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ዕድገት እንዳይሰጡ እገዳ ተጥሎባቸዋል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ከታህሳስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በየትኛውም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የተሰጠ እና የሚሰጥ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ዕድገት ተቀባይነት እንደማይኖረው አሳውቋል፡፡

ከጥቅምት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ የነበረውንና በትግበራ ወቅት ክፍተት የታየበት “የአካዳሚክ ሠራተኞች የደረጃ ዕድገት መመሪያ” በመሻሻል ላይ እንደሚገኝ ሚኒስቴሩ አስታውሷል፡፡

በዚህም ማሻሻያው ተጠናቆ ለሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እስከሚላክ ድረስ በሁሉም ተቋማት የፕሮፌሰርነት ዕድገት አሰጣጥ ለጊዜው መታገዱን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ “አንዳንድ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ክልከላውን በመጣስ፣ መመሪያውን ባልተከተለ፣ ግልጽነት በጎደለው፣ ወጥነት በሌለው እና ከትምህርት ጥራት ማስጠበቂያ ሪፎርሞች ጋር በሚጣረስ መልኩ የፕሮፌሰርነት ዕድገት መስጠት እንደቀጠሉ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ ገልጸዋል፡፡

ከታህሳስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በየትኛውም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የተሰጠ እና የሚሰጥ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ዕድገት ተቀባይነት እንደማይኖረው የገለፀው ትምህርት ሚኒስቴር፤ የተቋማቱ ከፍተኛ አመራር አካላት እና የሥራ አመራር ቦርድ የተሻሻለው መመሪያ ተጠናቅቆ እስኪደርሳችሁ ድረስ በትዕግስት እንዲጠብቁም ጠይቋል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የጥምህርት ጥራት እየቀነሰ መጥቷል በሚል የመምህራን ጥራትን ማሳደግ፣ የፈተና አሰጣጥ እና ሌሎች የጥራት ማስጠበቂያ መንገዶችን እየተከተለ ይገኛል፡፡

ለመምህራን ጥራት ልዩ ትኩረት እንደተሰጠ ትምህርት ሚኒስቴር ከዚህ በፊት የገለጸ ሲሆን የተለያዩ ስልጠናዎችን ለመመህራን በተለያዩ ፕሮግራሞች እንደሚሰጡም ተገልጿል፡፡

የትምህርት ቤቶችን ጥራትም ለማሳደግ እየተሞከረ ነው የተባለ ሲሆን አዳሪ ትምህርት ቤቶችን በስፋት ይገነባሉም ተብሏል፡፡

ልዩ ወይም አዳሪ ትምህርት ቤቶች ከሌሎች መደበኛ ትምህርት ቤቶች ጋር ሲነጻጸሩ የተሻለ ጥራት ያላቸውን ተማሪዎች በማፍራ ላይ ናቸው ተብሏል፡፡

ለአብነትም በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም አዳሪ ትምህርት ቤቶች ብሔራዊ ፈተና ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች ማሳለፍ ሲችሉ በሌሎች መደበኛ ትምህርት ቤቶች ከተፈተኑ ተማሪዎች መካከል የማለፊያ ውጤት ያመጡት ከ5 በመቶ በታች ናቸው፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *